ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እየተገበረ ያለውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚኖርበት ተገለጸ

You are currently viewing ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እየተገበረ ያለውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚኖርበት ተገለጸ

AMN ሰኔ 20/2017

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እየተገበረ ያለውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አጠናክሮ እንዲያስቀጥል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የባንኩን የ2017 በጀት ዓመት የ11 ወራት የሥራ አፈፃፀም ገምግሟል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የተቋሙን የገንዘብ ፖሊሲ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ስለተወሰዱ እርምጃዎች፣ የውጭ ምንዛሬ ሪፎርሙ ያስገኘውን ውጤት ጨምሮ የባንኩን የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል።

በማብራሪያቸው ተለዋዋጩ የአለም ጂኦ ፖለቲካ የሀገራትን የኢኮኖሚ ዕድገት ኢ-ተገማች ማድረጉን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ይህን ተግዳሮት በመቋቋም ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችሉ የሪፎርም ተግባራት ማከናወኗን ገልጸዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የኢኮኖሚ ጫናን በመቋቋም በፊስካልና በገንዘብ ፖሊሲ እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ ግኝት ውጤታማ ስራ አከናውናለች ብለዋል።

የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት በኩል ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተው፣ ባንኩ በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ምንም አይነት ብድር ለመንግስት አለመስጠቱን አመልክተዋል።

ከ50 ዓመታት በላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሲደረግበት የነበረው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርዓት በገበያ እንዲወሰን መደረጉም ትልቅ ስኬት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

በዚህም በህጋዊ ገበያውና በትይዩ ገበያው መካከል የነበረውን ከፍተኛ ልዩነት በማጥበብ ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው የውጭ ምንዛሬ እንዲጨምር ማድረጉን ነው ያብራሩት።

በአሁኑ ጊዜ የባንክ ዘርፉ በሁሉም መመዘኛዎች ጤናማ የሚባል መሆኑንም ነው ያስረዱት።

በባንኮች መካከል ያለው እርስ በእርስ የመበዳደር ምጣኔና የውጭ ምንዛሬ ክምችታቸው መጨመሩንም ተናግረዋል።

ባለፉት 11 ወራት የውጭ ምንዛሬ ግኝቱ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንና የመንግስት የውጭ ዕዳ የመክፈል አቅም በዚያው ልክ ማደጉን አብራርተዋል።

በምክር ቤቱ የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ በበኩላቸው፣ ባንኩ በተለያዩ ዘርፎች ያከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች የኢኮኖሚ መረጋጋት እንዲፈጠር ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።

ባንኩ በበጀት ዓመቱ አዋጆችን በማሻሻል በተለያዩ ዘርፎች ያከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች የተመዘገበባቸው መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው በጠንካራ ጎን መውሰዱን አንስተዋል።

በተለይም የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል ለመንግስት የሚሰጠውን ብድር ማስቀረት መቻሉ ትልቅ ውጤት አምጥቷል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብና መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችቱ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቡ የሪፍርሙ ውጤት ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review