በአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የተገነቡ 107 የህዝብ ንጽሕና መጠበቂያ ቤቶች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
ፅዱ ከተማን ለመፍጠር የማህበረሰብ መንገድ ዳር ንፅህና መጠበቂያ ቤቶች ለመዲናዋ ነዋሪዎች የሚኖራቸው አበርክቶ ከፍተኛ ነው ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ባለሙያ አቶ ጸዳሉ መሰለው፣ የኮሪደር ልማቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የተገነቡ 107 የህዝብ ንጽህና መጠበቂያ ቤቶች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸው፣ ይህም በከተማዋ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የንፅና ቤቶች ቁጥርን 384 እንዲደርሱ አስችሏል ብለዋል።
በተለያዩ ባለድርሻ አካላትና በቢሮው በጀት የተገነቡት የህዝብ ንፅህና መጠበቂያ ቤቶቹ ለአረጋውያነ፣ ለህፃናትና ለአካል ጉዳተኞች አካታች ሆነው የተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ በርካታ የንጽሕና መጠበቂያ ቤቶች ወደ አገልግሎት እንደሚገቡም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የኮሪደር ልማት በሌለባቸው አካባቢዎች ላይ የጤና ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የህዝብ ንጽሕና መጠበቂያ ቤቶችን እየገነባ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣዩ ዓመትም በቢሮው በኩል 100 የህዝብ የንጽሕና መጠበቂያ ቤቶች እንደሚገነቡ ተናግረዋል።
ማህበረሰቡ በህዝብ ንጽህና መጠበቂያ ቤቶች መጠቀም እንዲችል በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራም፣ መንገድ ላይ የመጸዳዳት ድርጊት መቀነሱን ገልጸዋል።
በመዲናዋ ከዚህ ቀደም 250 የህዝብ ንጽሕና መጠበቂያ ቤቶች እንደተገነቡ እና በኮሪደር ልማቱ ደግሞ 57 ማህበራት ተደራጅተው እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የንፅህና መጠበቂያ ቤቶቹ ከ2 ሺህ 5 መቶ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠራቸውም ባሻገር በከተማዋ ገፅታ ላይ ተጨማሪ ውበትን መፍጠር ችሏል ያሉት አቶ ፀዳሉ፣ ለንብረቱ ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ ማድረግ ከነዋሪው ይጠበቃል ብለዋል::
በሚካኤል ህሩይ