ብሔራዊ ቤተ-መንግሥትና አንድነት ፓርክ ተደብቀው የቆዩ የኢትዮጵያውያን ቅርሶችንና የማንነት መገለጫዎችን በውብ ገፅታ ለዓለም የገለጡ መሆናቸውን የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎች በአዲስ አበባ የተገነባውን አንድነት ፓርክና ብሔራዊ ቤተ-መንግስት ጎብኝተዋል።
ጉብኝቱን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሀገር ሽማገሌዎች እንደገለጹት፥ መንግሥት የኢትዮጵያን ውብ ቅርስና ታሪክ በማደስ የሚያኮራ ስራ ሰርቷል።
ሀደ ሲንቄ ሸምሲያ ጉተማ በሰጡት አስተያየት ለትውልድ የሚሻገሩ ድንቅ የልማት ሥራዎች ማየታቸውን አንስተው፥ አንድነት ፓርክና ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የኩራት መገለጫዎቻችን ናቸው ብለዋል።
ለዘመናት ተደብቀው የቆዩትን ቅርሶች በውብ ገፅታ ለማየት ትልቅ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቅሰው፥ ይህም የኢትዮጵያን የስልጣኔ ታሪክ አጉልቶ ለዓለም የገለጠ በመሆኑ ኮርቻለሁ ነው ያሉት።
የሁሉንም ብሔር ብሔረሰብ ባህልና ቅርስ በአንድ ላይ አካተው የያዙ መሆናቸውም የሀገራዊ አንደነታችን ምልክት እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር የአፍረንቀሎ አባገዳ ዋና ፀሃፊ ጉልላት ደምሴ በበኩላቸው የብሔራዊ ቤተ-መንግስት እድሳት የኢትዮጵያን ታሪክና ቅርስ በአግባቡ ሰንዶ ማስቀመጥ ያስቻለ ነው ብለዋል።
አዲስ አበባም በኮሪደር ልማት ውብና ጽዱ ሆና በማየታቸው መደነቃቸውን ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ተወካይ አቶ ካሳሁን ከበደ በበኩላቸው አዲስ አበባ በፈጣን ለውጥና እድገት ላይ መሆኗን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
የቤተ-መንግስት እድሳት ስራው ታሪክና ቅርስ እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ገልጸው በለውጡ ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ለኢትዮጵያ እደገት ትልቅ ተስፋ ናቸው ብለዋል።
በመዲናዋ አዳዲስ ልማቶችንና ነባር ቅርሶችን በአንድነት ያሰናሰለ ድንቅ የልማት ሂደት እንደተመለከቱ የተናገሩት ደግሞ በሲዳማ ክልል የሀገር ሽማግሌና የሃይማኖት መምህር ፓስተር ቦጋለ ወልደሃና ናቸው።
መንግሥት ብሔራዊ ቤተ መንግሥትና አንድነት ፓርክን ውብ አድርጎ በማደስ ለአዲስ አበባ ተጨማሪ ውበት ለትውልዱ ደግሞ የታሪክና የቅርስ ውርስ በተገቢው መንገድ ማስተላለፉ የሚያኮራ ነው ብለዋል።
ይህም የኢትዮጵያን ከፍታ እውን በማድረግ በኩል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ነው ያብራሩት።
የአፋር ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ተወካይ ዑመር አሊ በአዲስ አበባ የተከናወኑ የኮሪደር ልማቶችና የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች የኢትዮጵያን ቀደምትነት የሚገልጹ እሴቶችን የያዙ መሆናቸውን መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ተመሳሳይ የልማትና የቅርስ ጥበቃ ሥራዎች በሁሉም አካባቢ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የጠቆሙት።