ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች የተከየኑበት ማህበረሰብን እሴትና ዕውቀት አንጥሮ በማውጣት ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ ማህበረሰቡን በማቀራረብ፣ አብሮነትን በማጎልበትና የወል ተግባቦትን በማጠናከር ረገድም ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በቋንቋና በባህል የሚለያዩ ሰዎች በኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች አማካኝነት ወደ አንድነት ይመጣሉ። በጋራ እሴቶቻቸውና ርዕያቸው ዙሪያ ይሰባሰባሉ፡፡ በዚህ ዓምድም ኪነ ጥበብ (በተለይ ሥነ ጽሁፍ፣ ሙዚቃና ፊልም) ብዝሃ-ባህልን በማጐልበትና የጋራ መግባባትን በመፍጠር ረገድ ያላትን ሚና በጨረፍታ ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡
ብዝሃ-ባህል እና ኪነ ጥበብ
የኪነ-ጥበብ ስራዎች፣ ሰዎች ከራሳቸው ባህልና ቋንቋ ውጪ ያለውን ማንነትና አመለካከት እንዲረዱ ያደርጋሉ፡፡ ከሌሎች ሰዎች እና ከተለያየ ሀሳብ ጋር ፊት ለፊት ያገናኛሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ሰዎች ዓለምን ከራሳቸው ባህል ውጪ ማየት እንዲችሉ እና አብሮነትን እንዲያጠናክሩ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከተለያዩ ባህሎች መልካም እሴቶችን በመውሰድ ለመማር እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ ይህ ሂደት ደግሞ የወል ተግባቦትን በመፍጠር በተለይ በሀገር ጉዳይ ላይ የጋራ አረዳድና ርዕይ ለመቅረጽ ትልቅ ሚና አለው፡፡
ኪነ ጥበብ ከተለያዩ ባህሎች የመጡ ሰዎች በሙዚቃዎች፣ በፊልሞች፣ ስዕሎች እና የስነ ጽሁፍ ሥራዎች አማካኝነት እርስ በእርስ እንዲግባቡ እና እንዲረዳዱ ያግዛል። ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች እና ባህሎች ጋር ከሚዛመዱባቸው እና ከሚተዋወቁባቸው መንገዶች መካከል አንዱ ኪነ ጥበብ ነው። በዚህ ምክንያት አንዱ የሌላውን ባህልና ዕሴት ክብር በመስጠት የጥበብ ስራው አካል ስለሚያደርገው የወል ተግባቦትና ትርክት እንዲጎለብት ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡
‘ዘ ዴይሊ ጋርድያን’ የተሰኘው ገጸ-ድር፣ “The Impact of Art on Society” በሚል ርዕስ በወርሃ ሐምሌ 2023 ባስነበበው ጽሁፍ፣ ጥበብ ከጥንት ጀምሮ የሰው ልጅ የሥልጣኔ ዋና አካል ሆኖ የኖረ፣ የመግባቢያ እና የማሰቢያ ዘዴ ሆኖ ያገለገለ የሰው ልጆች ባለውለታ ነው። ከጥንታዊ የዋሻ ሥዕሎች እስከ ብሉይ (ክላሲክ) የሆኑ ድንቅ የፈጠራ ሥራዎች፣ እንዲሁም አሁን እየኖርንበት ባለው የዲጂታል ዓለም ጭምር የጥበብ ሥራዎች ወንድማማችነትና አብሮነትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እንደተጫወተ ያትታል፡፡
የባህል (ፎክለር) እና ኪነ ጥበባዊ ጉዳዮች ተመራማሪ ወሰን ባዩ (ዶ/ር)ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ የባህል ብዝሃነት በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ያሉ የተለያዩ ወጎችን፣ እምነቶችን እና ልማዶችን በማክበር የሰውን የህይወት ልምድ ይበልጥ የሚያሳድግና ውበትን የሚጨምር መሰረታዊ ገጽታ ነው። ኪነ ጥበባት ደግሞ ልዩ ማንነት የሚያንፀባርቁ የጥበብ ዕሴቶችና አገላለጾች መድረክን በማመቻቸት የባህል ብዝሃነትን በማስተዋወቅ እና በመጠበቅ በኩል ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡ እንደ ሲኒማ፣ ሙዚቃ፣ ውዝዋዜ፣ የዕይታ ጥበባት፣ ስነ- ጽሁፍ እና ቴአትር ባሉ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች አማካኝነት ጥበባት ባህላዊ መግባባትን ለማስተዋወቅና አዎንታዊ ተግባቦትን ለማዳበርና የወል ሀገራዊ ምናብ በመቅረጽ ኹነኛ መሳሪያ ሆነው እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል፡፡

‘ዲስከቨር ወክስ’ ገጸ-ድር በፈረንጆቹ 2023 ባወጣው አንድ መረጃ መሰረት፣ የባህል ብዝሃነትን በማስተዋወቅና ውበትን በማጉላት ረገድ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ከሚጫወቱት ቁልፍ ሚና አንዱ የተለያዩ ባህላዊ አመለካከቶች በፈጥራ ስራዎች አማካይነት እንዲወከሉ (represent) በማድረግ ነው። አርቲስቶች የአንድን ማህበረሰብ የሚገልጹ እሴቶችን፣ እምነቶችን እና ወጎችን በፈጠራ አጎልብቶ በማንፀባረቅ የባህላቸውን ምንነት በስራዎቻቸው የማሳየት ችሎታ አላቸው። እነዚህን ልዩ ልዩ ውክልናዎች በማሳየት፣ በተለያዩ ባህሎች መካከል አገናኝ ድልድዮችን ያንጻሉ፡፡ በዚህም ከተለያዩ አስተዳደግ በመጡ ግለሰቦች መካከል የመተሳሰብ እና የእርስ በእርስ ተግባቦት ስሜት እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ፡፡ ይሄ ደግሞ በተዘዋዋሪ በሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ገንቢ ሚና ይጫወታል ሲል ገጸ-ድሩ ያብራራል፡፡
ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ስራዎች ከተለያዩ ባህልና ማህበረሰብ በመጡ ግለሰቦች መካከል የእርስ በእርስ መገነዛዘብና መተሳሰብን የማሳደግ ዕምቅ አቅም አላቸው። እንደ ሙዚቃ፣ ስነ-ጽሁፍ፣ ቴአትር እና የእይታ ጥበባት ባሉ የተለያዩ የጥበብ ዓይነቶች ሰዎች ከሌሎች ባህሎች ልምዶች እና ታሪኮች መማር ብቻ ሳይሆን ዕሴትንም የመጋራት ዕድል ይፈጥራሉ። ይህም የእሴቶች መወራረስና የጋራ ማንነት በመፍጠር ረገድ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ሚናቸው ትልቅ መሆኑን ያመላክታል የሚሉት ወሰን ባዩ (ዶ/ር)፣ ይህ ሚና ብዙሃኑን ከማዝናናት ባሻገር ስለ ራሳችን በጥልቀት እንድናውቅና በሀገራዊ ጉዳይ ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንድናደርግ ያስችላል ብለዋል፡፡
በብዝሃ-ባህል ያጌጠችው ኢትዮጵያ እና ኪነ-ጥበብ
ሀገራችን ኢትዮጵያ የረጅም ዓመት የኪነ ጥበብ ታሪክ አላት፡፡ በዚህ ሁሉ ዘመን ኪነ ጥበብን በመጠቀም ስለ ህዝቦች አብሮነት ተሰርቷል፡፡ ስለ ፍቅር ተዘምሯል፡፡ ስለ ሀገር ፍቅርና መተሳሰብ ተገጥሟል፡፡ ውስንነት ቢኖርም ሕብራዊ ባህሎችና እሴቶችን አጉልተው የሚያሳዩ ፊልሞች ለእይታ በቅተዋል። በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ቅርሶችንና እሴቶችን የሚያወሱ ሙዚቃዎች ለአድማጭ ጆሮ ደርሰዋል። ብዙም ትኩረት ያላገኙ ማህበረሰባዊ እሴቶችን ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ መጽሐፍትም ለተደራሲያን ቀርበዋል፡፡
ከእነዚህ የጥበብ ስራዎች መካከል በተለይ የደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታ ስራዎች ካነሳነው ርዕሰ-ጉዳይ ጋር ጥብቅ ትስስር አላቸው፡፡ ፍቅረማርቆስ ደስታ በተለይም የሐመር ሕዝብ ባህል ላይ ባተኮሩት እጅግ ተወዳጅ ተከታታይ ‘ኤትኖግራፊክ’ ልብወለዶቹ ይበልጥ ይታወቃል፡፡ በደቡብ ኦሞ ቆይታው ከሐመር ማህበረሰብ ጋር ኖሮ ያየውንና የሰማውን በጥልቀት አጥንቶ፣ በኪናዊ ፈጠራ አስውቦ ድንቅ ልብወለዶችን ለተደራሲያን አቅርቧል፡፡ “ከቡስካ በስተጀርባ”፣ “ኢቫንጋዲ”፣ “የዘርሲዎች ፍቅር”፣ “Land of the Yellow Bull”… ከፈጠራ ልብወለድ ስራዎቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በእነዚህ የልብወለድ ድርሰቶች ውስጥ በተለይ የሐመር ማህበረሰብ ባህል፣ እሴቶችና ያልታዩ ታሪኮቻቸውን በማሳየት የኪነ ጥበብ ሃይልን በሚገባ ያስመሰከረ ደራሲ ነው፡፡ ስለ ሐመር ማህበረሰብ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የውጭ ተመራማሪዎች ጭምር እንዲሳቡ ያደረገ አጋጣሚም ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ስነ ጽሁፋዊ ስራዎች ብዝሃ ባህልን አጉልቶ በማሳየት፣ የወል እሴቶችን አንጥሮ በማውጣትና በማህበረሰቡ መካከል መልካም መስተጋብርን በመፍጠር ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው፡፡
የፍቅረማርቆስን ‘ከቡስካ በስተጀርባ’ የተሰኘው ተወዳጅ ድርሰቱን ተከትሎ እውቁ ሙዚቀኛ ጎሳዬ ተስፋዬ “ኢቫንጋዲ” የተሰኘ ሙዚቃ ለአድማጭ ማድረሱ ይታወቃል፡፡ የሐመር ማህበረሰብ ባህልና እሴቶችን ፍቅርን መነሻ በማድረግ በዚህ የሙዚቃ ሥራ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ ይሄ ሙዚቃ እስከዛሬ ድረስ እጅግ ከሚወደዱ ሙዚቃዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የፍቅረማርቆስ ድርሰቶችና ኢቫንጋዲ የተሰኘው ሙዚቃ የሐመር ማህበረሰብን ባህልና እሴቶች እንዲታወቁና በባህሎች መካከል የወል ተግባቦት እንዲኖር በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን አይተኬ ሚና መጫወት መቻላቸውን ወሰን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ወሰን (ዶ/ር) በማብራሪያቸው፣ የወል እሴትን አጉልቶ በማሳየትና የጋራ አረዳድ በመፍጠር ረገድ ከሀገራችን የኪነ ጥበብ ስራዎች መካከል ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በ1860ዎቹ የሴቶች የመብት ጥያቄዎችን ይዛ በመነሳት የጉራጌን ማህበረሰብና ባህል የሞገተችው የቃቄ ወርድወት ህይወትና አስተሳሰብ የሚያንጸባርቀው ቴአትርና ድርሰት፣ በኢትዮጵያ የሕብረተሰቡን ማህበራዊ መስተጋብርና ኢኮኖሚያዊ መሰረት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው የታላቁ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ‘ፍቅር እስከ መቃብር’ ድርሰትና ተከታታይ ድራማ እንዲሁም ከ1960ዎቹ በፊት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኘው የሱጴን መልክዓ-ምድርና የማህበረሰቡን አኗኗር የሚያሳየው የዕውቁ ደራሲ የበዓሉ ግርማ ‘ሀዲስ’ የተሰኘው የፈጠራ ድርሰት ላነሳነው ርዕሰ-ጉዳይ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የኪነ ጥበብ ስራዎች አንዱ ማህበረሰብ የሌላውን ዕሴት እንዲያውቅና እንዲማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ብለዋል፡፡
ሌላው ካነሳነው ሃሳብ ጋር አብሮ የሚሄድ አንድ ፊልም እናክል፡፡ የፊልሙ ርዕስ ‘ትዝታህ’ ይሰኛል፡፡ የፊልሙ መቼት ሲዳማ ውስጥ ሲሆን፣ ዋነኛ ጭብጡን ደግሞ ፍቅርና ትዝታ ላይ አድርጓል። ታዋቂዎቹ የሀገራችን ተዋንያን ግሩም ኤርሚያስና መሀመድ ሚፍታ በመሪ ተዋናይነት በተሳተፉበት በዚህ ፊልም ላይ፣ በእግረ-መንገዳችን የሲዳማን ባህል፣ እሴትና ለአካባቢ ጥበቃ ያላቸው ትልቅ እሴት በብዙ እንድንማር የሚያደርግ ነው፡፡
በአጠቃላይ ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ስራዎች የሚከየኑት ለሰዎች፤ የሚከይኑትም ሰዎች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፈጠራ ስራዎች በባህሪያቸው ሕዝባዊ ናቸው፡፡ ሰውን ዋነኛ ነገረ-ጉዳይ አድርገው ስለሚነሱ ተጽዕኖቸው የቋንቋን ድንበር ይሻገራል። ምክንያቱም የጥበብ ስራዎች ለሰው ልብ እጅግ የቀረቡ ናቸው። የተከየነበትን ባህል፣ ቋንቋና አውድ ሳንረዳው እንኳን ዕሴትን እንድንጋራ፣ የወል ማንነታችን እንዲጎለብት እና የእርስ በእርስ መከባበር እንድናዳብር ስለሚያደርጉ ትልቅ ትኩረት ይሻሉ፡፡
በአብርሃም ገብሬ