ህይወት አድኑ በጎነት

You are currently viewing ህይወት አድኑ በጎነት

     ደም ከመለገስ የሚያግደኝ ነገር የለም

                                               ሲስተር አሰጋሽ ጎሳ ለ121 ጊዜ ደም የለገሱ

ለማያውቁት ሰው በማያውቁት መንገድ የመኖር ምክንያት ከመሆን በላይ የሚያስደስት ምን ነገር አለ፡፡ ዛሬ በሽርፍራፊ ደቂቃዎች ውስጥ የለገሱት ደም ለአንድ እናት ወይንም ህፃን የመኖር ሰበብ ሊሆን ይችላል። ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ማትረፍን የመሰለ ታላቅ ነገር ደግሞ ከየት ይገኛል፡፡

በተለያዩ ሆስፒታሎች በተለይም በወሊድ ምክንያት ደም አጥሯቸው ሕይወትን ለመስጠት ሕይወታቸውን የሚያጡ እናቶች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ታዲያ በዚህ ወቅት ቅን ልቦና የተቸራቸው፣  ሰውን ለመርዳት መስፈርቱ ሰው መሆን ብቻ ነው የሚለው እውነት የገባቸው የበጎነት ተምሳሌት የሆኑ ሰዎች ደማቸውን ለግሰው የበርካቶችን ሕይወት ታድገዋል፡፡ ሕይወትን ለመስጠት እናት ሕይወቷን እንዳታጣም ምክንያት ሆነዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ምስክር የሚሆኑን በኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ የትምህርት እና ቅስቀሳ ባለሙያ የሆኑት ሲስተር አሰጋሽ ጎሳ ለ121 ጊዜ ደም በመለገስ ‹‹ለወገን ደራሽ ወገን ነው›› የሚለውን አባባል በተግባር ያሳዩ ጀግኒት ናቸው፡፡

ዛሬ ላይ ለ121ኛ ጊዜ ደም ለመለገስ ምክንያት የሆናቸውን አጋጣሚም ከአዲስ ልሳን ጋር በነበራቸው ቆይታ አጫውተውናል፡፡ የቁም ነገሩ መነሻም በደም ባንክ ባለሙያ ሆነው እየሰሩ በነበረበት ወቅት ከክፍለ ሀገር በወሊድ ምክንያት ባለቤቱን ደም እየፈሰሳት ጥቁር አንበሳ ለህክምና ይዞ የመጣ አባወራ እንደሆነ ያስታውሳሉ፡፡

ይህ አባወራ ‹‹ከሆስፒታሉ ቁልቁል አየሮጠ በመምጣት የልጆቼ እናት ልትሞትብኝ ስለሆነ እሷ ከምትሞት እኔ ልሙት ደም መስጠት የሚገድል እንኳን ቢሆን እሷ ከምትሞት እኔ ልሙት›› ብሎ እንደጠየቃቸው ያወሳሉ፡፡

ታዲያ ያኔ ውስጣቸው ባለመቻሉ ያንተን ፋንታ እኔ እሰጣለሁ! በማለት በ1984 ዓመተ ምህረት የመጀመሪያውን ልገሳ እንዳደረጉ የሚናገሩት ሲስተር አሰጋሽ በዚህ አንድ አጋጣሚ የተጀመረው የደም ልገሳ የበጎ ፍቃድ ተግባርም፣ ሶስት አስርት ዓመታትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል፤ ደም የሚያስፈልጋቸው ወገኖች እስካሉ ድረስም ደም ከመለገስ የሚያግደኝ ነገር የለም ይላሉ፡፡

የደም ልገሳ በቤተሰባቸውም የተለመደ ቅዱስ ተግባር መሆኑን የሚናገሩት ሲስተር አሰጋሽ፣ ቤታቸው ሆስፒታል አካባቢ በመሆኑ፣ ወላጅ እናታቸውም ደም የተቸገሩ ወገኖች ሲያወሩ ሰምተው ምንም ግንዛቤ ባልነበረበት ወቅት እንኳን ደም እንደለገሱ ያስታውሳሉ፡፡

እንደ ከተማ ያለውን የደም ልገሳ እንቅስቃሴ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡን ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስተባባሪያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳዊት ሙልጌታ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፃ የደም ልገሳ መርሐ ግብር ክረምት ከበጋ ከሚከናወኑ የበጎ ፍቃድ ተግባራት አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም በ2017  ዓመተ ምህረት የክረምት መርሐ ግብርም በአስራ አንዱም ክፍለ ከተማ  40 ሺህ የሚጠጉ በጎ ፍቃደኞችን በማስተባበር ደም የማሰባሰብ ስራ ተጀምሯል፡፡

በኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታየ  እንደ ሀገር ደም የመለገስ ባህል ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ መምጣቱን አስታውሰው፤ማንኛውም ዕድሜው ከ18 እስከ 65 ዓመት የሆነ እና ክብደቱ ከ50 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን “ጤናማ” ግለሰብ በየ3 ወሩ በቋሚነት ደም ለመለገስ ብቁ መሆኑን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ የክልል ከተሞችን ጨምሮ 59 የሚጠጉ የደም ባንኮች የሚገኙ ሲሆን፣ የበዓል ቀናትን ጨምሮ በሳምንት 7 ቀናት ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ድረስ የለጋሾችን ደም ለመቀበል ክፍት ሆነው ይጠባበቃሉ።

በእነዚህም ዓመቱን ሙሉ ከሳምንት እስከ ሳምንት ያለምንም ማቋረጥ ደም እንደሚሰበሰብ ያስታወሱት አቶ ሀብታሙ በአዲስ አበባም ከተመረጡ ደም ተቀባይ የጤና ተቋማት ባሻገር  2 ቋሚ እና 11 ተንቀሳቃሽ የደም መሰብሰቢያ ክሊኒኮች በቋሚነት ደም የማሰባሰቡን ስራ እንደሚሰሩም ይገልጻሉ አቶ ሀብታሙ።

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለፃ በክረምት ለሚያጋጥመው የደም እጥረት እንደዋነኛ መንስኤ የሚነሳውም ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ደም ለጋሽ ተማሪዎች በመሆናቸውና ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው እንደሆነና ሌሎችም አብዛኛዎቹ በበጋ ደም የሚሰበሰብባቸው ተቋማት መዘጋታቸው ነው፡፡ ይህን ክፍተት ለመሙላት ሲባል የኢትዮጵያ በጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ማህበር አስተባባሪነት በከተማዋ በተመረጡ አደባባዮችና ከ15 ባላነሱ አካባቢዎች ድንኳን ተተክሎ ከጠዋት እስከ ማታ ደም የማሰባሰብ ስራ ይሰራል፡፡

በደም ልገሳ ላይ የሚሰራው የወጣቶች ማህበር ለህብረተሰቡ ደም መለገስ ስላለው ጥቅምና ተያያዥ ጉዳዮች በማስተማርና በማነሳሳት ረገድ አይነተኛ ድርሻ እንዳለው ይታመናል የሚሉት አቶ ሀብታሙ በተደረገው ሰፊ የንቅናቄ ስራም በያዝነው በጀት ዓመት አስራ እንድ ወር 378 ሺህ 500 ዩኒት ደም እንደሀገር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ወደ 60 ሺህ አከባቢ ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል።

በጎ ፍቃደኞች ደም ሲለግሱ ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት ከመታደጋቸው ባለፈ የደም ዓይነታቸውን ጨምሮ የጉበት፣ የኤች አይ ቪ፣ የአባላዘር እና የሌሎች በቫይረስ የሚተላለፉ በሽታዎች ምርመራ ውጤታቸውን አቅራቢያቸው ወደሚገኝ የደም ባንክ ቀርበው ከምክር አገልግሎት ጋር ለመውሰድ መቻላቸውም ሌላው ተጓዳኝ ጥቅም እንደሆነ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት በሚገኘው ደም ባንክ ደም ስትለግስ ያገኘናት ወጣት ቅድስት አሰፋ ደም መለገስ በሌሎች ህይወት ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ቀላል ተግባር መሆኑን ትናገራለች:: ደም መለገስ በደም እጦት በሞት አፋፍ ላይ ላሉ ህይወት መስጠት ነው የምትለው ወጣቷ ለጋሽ የራስ ተነሳሽነትና ፈቃደኝነት ብቻ በቂ እንደሆነ ነው ያረጋገጠችው።

ደም መለገሰ ከምንም በላይ የህሊና እርካታን እንደሚሰጥ የነገሩን ለ47ኛ ጊዜ ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ተስፋሁን ገብረመድህን ናቸው፡፡ ገና በለጋው እድሜያቸው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ደም በመለገስ ለወገን ደራሽነታቸውን ያረጋገጡት አቶ ተስፋሁን ደም መለገስ ለሰጭው ምንም ጉዳት የሌለው ለተቀባዩ ግን ህይወትን መታደግ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ደም መለገስ በተለይ ለወላድ እናቶች፣ በከባድ የጤና እክል ለሚሰቃዩ፣ ቀዶ ጥገና ለሚያደርጉ  ወይም  በአደጋ ምክንያት ከፍተኛ የደም መፍሰስ ያጋጠማቸው ሰዎችን ህይወት ለመታደግ የሚያስችል በጎ ተግባር በመሆኑ ሲለግሱ ከፍተኛ የሆነ የአዕምሮ እርካታ እንደሚሰጣቸው ገልፀዋል፡፡

ደም በመለገስ የሚደረግ ተባባሪነት ውስጥ ተመርምሮ የራስን ጤና ማረጋገጥ ከመቻሉም ሌላ በርካታ የጤና ጥቅሞች ስላሉት እድሜያቸው እስከፈቀደ ድረስ ያለማቋረጥ ለመለገስ ለራሳቸው ቃል መግባታቸውንና ሌሎች ወገኖችም ደም በመለገስ ወገናዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በያዝነው በጀት ዓመት አሁን እየተገባደደ ያለውን ሰኔ ወርን ጨምሮ እስከ መስከረም 30 እንደሀገር 513 ሺህ ዩኒት ደም ይሰበሰባል ተብሎ የታቀደ ሲሆን እስከአሁንም 80 በመቶ የሚሆነው ተሰብስቧል፡፡ ባሉት ቀሪ ቀናት ደግሞ እቅዱን ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን  ከኢትዮጵያ ደምና ህዋስ ባንክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሸዋርካብሽ ቦጋለ 

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review