የላፍቶ ቁጥር ሁለት የገበያ ማዕከል በቅርቡ ለአገልግሎት መብቃቱ ይታወቃል፡፡ ይህ ማዕከል፤ በተለምዶ ጋርመንት አትክልት ተራ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ በሚገኝ ሥፍራ ላይ ይገኛል፡፡ ከ8 ነጥብ 8 ሄክታር መሬት በላይ ያረፈ ነው። ማዕከሉ ሁለት ዘመናዊ ምርት ማቆያ መጋዘኖች፣ 9 የጅምላ ማከፋፈያዎች (ሞሎች) እና 159 ሱቆች አሉት፡፡
ማዕከሉ ለአገልግሎት ሲበቃ መርቀው የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ የላፍቶ ቁጥር ሁለት የገበያ ማዕከልን ጨምሮ እስካሁን በተገነቡት ማዕከላት ውስጥ 1037 ሱቆችና ግዙፍ መጋዘኖች አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፤ እነዚህ ማዕከላት የንግድ ትስስርን ለማሳለጥ፣ የግብይት ስርዓቱን ጤናማ ለማድረግ፣ አምራቾች ምርት ማከማቻና መሸጫ ቦታ ሳይቸገሩ የሚሸጡበት ሁኔታ ለመፍጠር፣ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያለው የከተማዋ ነዋሪ፣ የመንግስት ሠራተኛው እና ደሞዝተኛው የሚደርስበትን የኑሮ ጫና ለማቃለል ሁነኛ መፍትሔ እየሰጡ መሆናቸው በተግባር መረጋገጡን አንስተዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ተግባራት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚጨምሩ፣ የህዝብ እና የመንግስትን ግንኙነት የሚያሳድጉ በመሆናቸው ወደፊትም አስተዳደሩ ለሕዝቡ የገባቸውን ቃሎች በተግባር እየፈፀመ የሚሄድ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም የዚህን ማዕከል የሥራ እንቅስቃሴ ለመመልከት ወደ ሥፍራው አቅንቷል፤ በማዕከሉ በመገኘት የሥራ እንቅስቃሴውን ተዟዙሮ ተመልክቷል። ሸማች እና አምራች ነጋዴዎችን አነጋግሯል፡፡ የማዕከላቱ የበላይ ተቆጣጣሪ የሆነው የንግድ ቢሮ የሥራ ኃላፊዎችንም አስተያየት ተቀብሏል፡፡ እነዚህን የመረጃ ምንጮች በማጠናቀር ስለማዕከሉ የሥራ እንቅስቃሴ ምስል ይሠጣል ያለውን ፅሑፍ እንደሚከተለው አሰናድቷል፡፡
ነዋሪነታቸው በሀና ማርያም አካባቢ የሆኑት ወይዘሮ አበበች ከበደን፤ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በማዕከሉ ውስጥ ሲሸምቱ አገኘናቸው፡፡ እሳቸው ስለማዕከሉ አገልግሎት እና ስለምርቶቹ ሁኔታ እንደሚከተለው ሃሳባቸውን ሰጥውናል፡፡ “አኔ የገዛሁት አተር ክክ፣ ሽምብራ ክክ እና ጓያ ክክ ነው። እነዚህን ምርቶች እዚህ መጥተን ከመግዛታችን በፊት ውጪ ባሉ ነጋዴዎች የሚሸጡባቸውን ዋጋ አጣርተናል፡፡ ውጪ ባሉ ነጋዴዎች ሽምብራ እና ጓያ በተመሳሳይ በኪሎ 160 ብር ነው፡፡ አተር ደግሞ በኪሎ 220 ብር ነው፡፡ እዚህ ግን አንድ ኪሎ ሽምብራ 145 ብር፣ ጓያ አንድ ኪሎ በ135 ብር እንዲሁም አተር በኪሎ 180 ብር ገዝተናል፡፡”
“የጤፍ ዋጋም ተዘዋውረን ጠይቀናል። ጥራት ያለው ጤፍ ከውጪ ካለው በኪሎ ከ15 እስከ 25 ብር ቅናሽ እንዳለው አውቀናል፡፡ እዚህ በዋጋ ደረጃ የተሻለ ነው፡፡ ጥራቱም በጣም ጥሩ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በአትክልት ተራው በጣም ተጠቃሚ ሆነናል፡፡ አሁን ደግሞ የሰብል እና የጥራጥሬ ምርቶች የሚሸጡበት ማዕከል ለአገልግሎት በመብቃቱ በጣም ደስተኛ ሆነናል፡፡ አቅርቦቱ ከዚህም በላይም ቢሆን ጥሩ ነው፡፡” የሚሉት ወይዘሮ አበበች፤ ማዕከሉ ከሚኖሩበት ቅርብ አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ የበለጠ ተጠቃሚ መሆናቸውን አልሸሸጉም። “የፈለግነውን ምርት በየትኛውም ጊዜ ገዝተን ለመጠቀም የሚያስችለን ሁኔታ ከተማ አስተዳደሩ ስላመቻቸልን እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለአገልግሎት በበቃው የላፍቶ አትክልትና ፍራፍሬ መሸጫ ገበያ ማዕከል ተጠቃሚ መሆናቸውን በማንሳት፣ መንግስት ሸማች እና አምራቹን በቀጥታ ለማገናኘት እየሠራው ያለው ተግባር ለዜጎች ያለውን ትኩረት የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ከሁለት ጓደኞቻቸው ጋር ጥራጥሬ እና ምሥር ክክ ለመሸመት መጥተው በማዕከሉ ሲንቀሳቀሱ ያገኘናቸው ወይዘሮ ጀማነሽ አዳነ፤ በማዕከሉ ውስጥ ስላለው የምርት አቅርቦት፣ የጥራት እና የዋጋ ሁኔታ ከውጪ ካለው ጋር በማነፃፀር እንዲገልፁልን በጠየቅናቸው መሰረት ሀሳባቸውን እንዲህ አብራርተዋል፤ “የመኖሪያ አካባቢዬ ላፍቶ ነው፡፡ ወደዚህ የመጣሁት ምስር እና አተር ክክ ለመግዛት ነው፡፡ አመጣጤም በማዕከሉ እየቀረቡ ያሉ የግብርና ምርቶች ጥራት ያላቸው እና በዋጋቸውም ተመጣጣኝ የሚባል እንደሆነ ባገኘሁት መረጃ መሰረት ነው። መጥቼ በየመሸጫ ሱቆቹ ተዟዙሬ እንደተመለከትኩት፣ የተለያየ ዓይነት የሰብል እና የጥራጥሬ ምርቶች አሉ፡፡ ጥራታቸውም በጣም ጥሩ የሚባል ነው። ብዙ አማራጮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የጤፍ ምርት በጥራትም በዋጋም ውጪ ካለው የተሻለ ነው፡፡”
ወይዘሮ ጀማነሽ እና ጓደኞቻቸው በማዕከሉ ተዘዋውረው ባደረጉት ቅኝት የታዘቡት ነገር እንዳለም አልሸሸጉም፡፡ አንዳንድ ምርቶች ላይ የዋጋ ሁኔታ ውጭ በነጋዴዎች ከሚሸጠው ብዙም ልዩነት የሌለው መሆኑን፣ በንግድ ቢሮ ለመሸጫ ተብሎ የተለጠፈው የዋጋ ተመንን በማለፍ የመሸጥ አዝማሚያ ማየታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ይህንን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ “አንዳንድ ምርቶች ላይ በማዕከሉ የሚሸጠው በውጭ ካሉ ነጋዴዎች የመሸጫ ዋጋ ብዙም የተለየ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በተጨማሪ፤ በንግድ ቢሮ ከተለጠፈው የመሸጫ ዋጋ ዝርዝር ጨምረው የሚሸጡ አምራቾችም አጋጥመውኛል፡፡ ለምሳሌ ምሥር ክክ ለመግዛት ጠይቄ በኪሎ 300 ብር እንደሆነ ነው የተነገረኝ፡፡ የዚህ ምርት ዋጋ በውጪም ብዙ የተለየ አይደለም። ደግሞም በንግድ ቢሮ የመሸጫ ዋጋ ተብሎ የተለጠፈው በኪሎ 272 ብር ነው” ብለዋል፡፡
በንግድ ቢሮ ከተለጠፈው የመሸጫ ዋጋ ጨምረው እየሸጡ ነው ወደተባለው ሱቅ አምርተን ሁኔታውን ለመመልከት ሙከራ አድርገናል፡፡ በዕለቱ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎበታል የተባለውን የምስር ክክ ምርት በኪሎ 300 ብር ሂሳብ 75 ኪሎ የገዛ ነጋዴን አግኝተን አነጋግረናል፡፡ ነጋዴው፤ አቶ ተማም ኑረዲን ይባላል፡፡ የገዛውን ምርት በኪሎ 300 ብር እንደገዛ በመጠቆም፤ በሱቅ ችርቻሮ በኪሎ 310 ብር እየተሸጠ መሆኑን አንስቶልናል። ይህ እንዳለ ሆኖ፤ ከተለጠፈው የዋጋ ዝርዝር ከፍ አድርጎ ሲሸጥ የነበረው አምራች ነጋዴ ይህንን ለምን እንዳደረገ ላነሳንለት ጥያቄ፤ “በየዕለቱ የገበያው ዋጋ ልዩነት ስለሚያመጣ፤ በአንዳንድ ምርቶች ላይ የዋጋ ልዩነት ሊፈጠር ይችላል፡፡ በምሥር ክክ ላይ የታየው የዋጋ ልዩነት ከዚህ የመጣ ነው፡፡ ሌላው ምርት ላይ እንደዚህ ዓይነት ልዩነት የለም” የሚል ምላሽ ሰጥቶናል፡፡
ከላይ ያነሳነውን በምሥር ክክ ዋጋ ላይ ከታየው የዋጋ ልዩነት በስተቀር በማዕከሉ አጠቃላይ ያለው የሸማች እና የአምራች ነጋዴ መስተጋብር እጅግ የሰመረ መሆኑን መታዘብ ችለናል። በማዕከላቱ ያሉ ሱቆች በምርት ተሞልተው ተመልክተናል፡፡ ሸማች ከአንዱ ወደ ሌላው ሱቅ በመንቀሳቀስ ምርቶችን በጥራትም በወጋም አወዳድሮ የወደደውን የሚወስድበትና የሚገዛበትን ሁኔታ አይተናል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በመመደብ እየገነባ ለአገልግሎት ያበቃቸው የግብይት ማዕከላት ለሸማቹ ብቻ ሳይሆን ለአምራች አርሶ አደሮችም ትልቅ የገበያ አማራጭ የተፈጠረላቸው መሆኑን መስክረዋል፡፡
ወጣት ኃይሌ ወርቁ ፤ የመልካ ወጂ የሰብል አምራች እና አቅራቢ ድርጅት የሥራ ባልደረባ ነው፡፡ እንደሱ ገለፃ፤ ድርጅቱ ምርቶቹን በአብዛኛው የሚያቀርበው በምስራቅ ሸዋ፣ መቂ፣ ቡልቡላ፣ ሞጆ አካባቢ ካሉት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች በማምረት ነው፡፡ ድርጅቱ ዋና ዋና የሰብል ምርቶችን (ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ጥራጥሬዎች፣ ቦሎቄ…) ጨምሮ አትክልትና ፍራፍሬዎችንም (አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ቲማቲም፣ ድንች፣ ካሮት፣ ጎመን…) በማምረት ለተጠቃሚዎች ያቀርባል፡፡ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ የገበያ መረጋጋትን ለማስቀረት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር በተጨማሪ ወደተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ይገኛል፡፡
መረጃውን ለመሰብሰብ እና የገበያውን እንቅስቃሴ ለመቃኘት በተገኘንበት ዕለት (ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም.) በድርጅቱ የቀረቡ የተለያዩ የሰብል ምርቶችን ዋጋ ጠይቀን ተረድተናል፡፡ በዚሁ መሰረት፡- ደረጃ አንድ ነጭ ጤፍ በኩንታል 12 ሺህ ብር ነው፡፡ ተመሳሳዩ ጤፍ በነጋዴዎች ከ14 ሺህ እስከ 14 ሺህ 500 ብር ይሸጣል፡፡ ቀይ ጤፍ እንደ ደረጃው ከ9 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር በኩንታል ለሽያጭ ቀርቧል። በቆሎ በኩንታል 2 ሺህ 500 ብር፣ ሽምብራ በኩንታል 10 ሺህ ብር፣ ስንዴ እንደ ደረጃው ከ6 ሺህ እስ 7 ሺህ ብር በኩንታል፣ ባቄላ ከ13 ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር በኩንታል እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ቦሎቄ በኪሎ ከ250 እስከ 300 ብር ለሸማች ቀርቧል፡፡
“ከአንድ ኪሎ ጀምሮ የፈለጉትን ያክል ምርት በየዓይነቱ መግዛት ይቻላል። ድርጅቱ የአቅርቦት ችግር የለበትም። በየሳምንቱ እስከ 500 ኩንታል ምርቶችን እያስገባ ይገኛል” የሚለው ወጣት ኃይሌ፤ ከዚህ ቀደም በገበያ ላይ ለምርቶች ዋጋ መናር ዋና ምክንያት በአምራች እና በሸማች (ተጠቃሚ) መካከል የደላሎች መግባት መሆኑን በማስታወስ፤ ደላሎች አላስፈላጊ ዋጋ እንዲጨመር ማድረጋቸውን አንስቷል። አሁን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁ ግዙፍ የገበያ ማዕከላት ደላሎችን ከገበያው ማስወጣት በመቻላቸው አምራቾች ምርታችንን ቀጥታ ከእርሻ በማምጣት ለሸማቹ እንዲደርስ የሚደረግበት ዕድል መፈጠሩን ተናግሯል፡፡
አቶ ምስጋናው ዲባ ይባላሉ፡፡ የእቴነሽ ቦጋለ የእርሻ ልማት ድርጅት የሽያጭ ሠራተኛ ናቸው፡፡ በላፍቶ ቁጥር ሁለት የግብይት ማዕከል በሚገኝ ሱቅ ምርቶችን እየሸጡ ነው ያገኘናቸው። እሳቸው ስለሥራ እንቅስቃሴው እንዲያስረዱን ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ፤ “ቁጥር አንድ የምርት መሸጫ ለሚ ኩራ የገበያ ማዕከል ላይ አለን፡፡ ጥራት ያላቸውንና ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን የጠበቁ ምርቶችን ነው ለተጠቃሚው የምናቀርበው። ስንዴ፣ ጤፍ እና ሌሎች የጥራጥሬ ምርቶችን በስፋት እናመርታለን፡፡ ምርቶቻችንን ለምርጥ ዘር ተጠቃሚ አርሶ አደሮች እና ለሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረብን እንገኛለን። ከዚህ ቀደም ምርቶቻችንን ለነጋዴ ነበር የምናስረክበው፡፡ የእኛ ምርት ለሸማቹ የሚደርሰው በቀጥታ አልነበረም፡፡ ደላላ እና ነጋዴዎችን አልፎ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በምርቱ ጥራትም ሆነ ዋጋ ላይ ተፅዕኖ እንዲፈጠር ያደርጋል” ብለዋል፡፡
አክለው እንዳስረዱት፤ አሁን ላይ ቀጥታ ምርቶችን ከእርሻ በማምጣት ለተጠቃሚው እያቀረብን እንገኛለን። የእርሻ መሬቶቻችን ያሉት በባሌ እና ጊኒር ነው፡፡ እነዚህ ምርቶች በማዕከሉ ለጉብኝት በተገኘንበት ዕለት (ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም.) የመሸጫ ዋጋቸው የነበረው፡- ቀይ ጤፍ እንደ ደረጃው በኩንታል ከ9 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር፣ ነጭ ጤፍ በኩንታል ከ12 ሺህ ብር ጀምሮ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ የላፍቶ ቁጥር ሁለት የግብይት ማዕከል ለአገልግሎት የበቃው በቅርቡ እንደመሆኑ መጠን፤ ብዙ ሸማች እየመጣ አይደለም፡፡ የምርት አቅርቦት በከፍተኛ መጠን አለ፡፡ ከዚህ የተሻለ ማቅረብም ይችላል፡፡ አምራቹ ምርቱን ለነጋዴ ከሚያቀርብ ይልቅ ለሸማቹ ማቅረብ በገንዘብ ከሚያገኘው ጥቅም በተጨማሪ ውስጣዊ ደስታንም ይጎናፀፋል፡፡
“አምራች ገበሬ ነኝ፡፡ በንፋስ ስልክ ቁጥር ሁለት የገበያ ማዕከል የሰብል ምርቶችን ለሸማች እያቀረብኩ እገኛለሁ። ለሸማቹ የማቀርባቸውን ምርቶች የማመርተው ምዕራብ አሩሲ ባለኝ የእርሻ መሬት ነው፡፡ ምርቶቼን ምንም ዓይነት ደላላ ሳይገባ በቀጥታ ነው ለሸማች የማቀርበው” የሚሉት አቶ በሽር ወሼ በበኩላቸው፤ በላፍቶ ቁጥር ሁለት የገበያ ማዕከል የከፈቱት የምርት መሸጫ ሱቅ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ሁለተኛው መሆኑን አንስተዋል፡፡ የመጀመሪያው በአቃቂ ቃሊቲ የገበያ ማዕከል ይገኛል፡፡
እሳቸው ከማያቀርቧቸው ምርቶች መካከል፡- ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ሽምብራ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ምርቶችን ቢያንስ በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት ለተጠቃሚዎች የሚያቀርቡት አምራች አርሶ አደሩ፤ ጤፍ በመኸር አምርተው ካነሱ በኋላ ድንች ወደማምረት እንደሚገቡ ገልፀዋል፡፡ ድንቹ እንደደረሰም ለሸማቹ በቀጥታ ያቀርባሉ። ስለዚህ ከሰብል እና ጥራጥሬ ምርት በተጨማሪ አትክልትና ፍራፍሬዎችንም አምርተው የሚያቀርቡበት ዕድል አለ። በእሳቸው ሱቅ ተገኝተን ባደረግነው ምልከታ በዕለቱ (ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም.) የቀረቡ ምርቶች የመሸጫ ዋጋቸው፤ አንደኛ ደረጃ ገብስ በኩንታል 9 ሺህ ብር፣ ቀይ ጤፍ ደረጃ አንድ 8 ሺህ 9 መቶ ብር፣ ነጭ ጤፍ ደረጃ ሁለት በኩንታል 11 ሺህ 500 ብር፣ ሽምብራ በኩንታል 10 ሺህ ብር እየተሸጠ መሆኑን አረጋግጠናል፡፡
“የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ባለፉት ዓመታት ከሠራቸውና ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ካደረጉ በርካታ የልማት ሥራዎች መካከል የግብይት ማዕከላት ይጠቀሳሉ፡፡ በቅርቡ ለአገልግሎት የበቃው የላፍቶ ቁጥር ሁለት ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው” ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ብርሃኑ፤ የላፍቶ ቁጥር ሁለት የግብይት ማዕከል በከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተመርቆ ለአገልግሎት ከበቃበት ዕለት አንስቶ አምራቾች ምርቶቻቸውን ለሸማቾች እያቀረቡ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ ሁሉም ሱቆች በሚባል ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ማዕከል የገቡ አምራቾች የተመረጡ እና ውጤታማ የተባሉ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ተግንብተው ለአገልግሎት የበቁ የገበያ ማዕከላት ግዙፍ፣ ዘመናዊ፣ አስፈላጊ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የሰብል ምርቶችን ለመገበያየት የሚያስችሉ ናቸው፡፡ መጋዘኖች እና ወፍጮ ቤቶችም አሏቸው፡፡ የላፍቶ ቁጥር ሁለት የገበያ ማዕከል ከሌሎች ለየት የሚያደርገው ራሱን የቻለ ግዙፍ ሞል አለው፡፡ ሞሉ፤ ሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንሰሳት ተዋፅኦ እንዲሁም የፋብሪካ ምርቶችን ለመገበያያነት የሚያገለግል ነው፡፡ ባንኮች እና የፋይናስ ተቋማትም በማዕከሉ አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ ያመቻቸ ነው፡፡ የአስተዳደር ቢሮዎችም አሉት፡፡
የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ የንግድ ቢሮ የገበያ ማዕከላትን እና ቁጥራቸው 214 ለሚደርሱ የእሁድ ገበያዎች (ሰንደይ ማርኬት) በየሳምንቱ አርብ አርብ ዕለት የዋጋ ተመን በማውጣት ይፋ ያደርጋል። ግብይቱም በወጣው የዋጋ ተመን የሚከናወን ይሆናል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ አስገንብቶ ለአገልግሎት ባበቃቸው የገበያ ማዕከላት የሚከናወነው ግብይት ከሌላው የግብይት ሥፍራ ወይም ከነጋዴው ከ15 እስከ 20 በመቶ የዋጋ ቅናሽ እንዲያደርግ ይጠበቃል፡፡ ከተተመነው የዋጋ ተመን ውጪ መሸጥ የተከለከለ ነው፡፡ አገልግሎቱ በተዘረጋው የአሠራር ሂደት መከናወን አለመከናወኑን በየጊዜው የሚከታተሉ የግብይት ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ችግር ሲፈጠር እነሱ ወዲያው መፍትሔ የሚሰጡ ይሆናል፡፡ የምርት እጥረት ካለ ለቢሮው በማሳወቅ መፍትሔ የሚሰጥበትን አግባብ ማበጀት ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ አምራች ነጋዴዎች ላይ ከሥርዓት ውጪ የሆነ ተግባር አይፈፀምም ማለት አይቻልም። ይህንን ሲፈፅም የተገኘ ነጋዴ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ በጀት በማውጣት ለአገልግሎት ያበቃቸው ማዕከላትን አምራቹ እንዲጠቀም የተደረገው ሸማቹ እንዲጠቀም በማሰብ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በግብይት ሥርዓቱ ላይ የሚታይ ችግር ካለ 24 ሰዓት በሚሠራው በነፃ የስልክ ቁጥር 8588 በመደወል ለቢሮው ማሳወቅ የሚቻል መሆኑን በመረዳት ሕብረተሰቡ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
በደረጀ ታደሰ