አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያለ ልዩነት ለተሻለ ነገ በጋራ የምንሰራው የሀገር ግንባታ አካል ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማን፤ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና በተገኙበት ተካሄዷል።
“በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉም ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿን በማስተባበር በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አብነት የሚሆን ስራ ማከናወኗን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዜጎችን በማሳተፍ፣ ለሀገራዊ ማንሰራራት ቁልፍ ሚና በመጫወት እንዲሁም ነገን አሻግሮ የተመለከተ መሆኑንም አብራርተዋል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በገዛ ፍቃዳቸው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያከናወኑት ስራም የመደመር አቅምን ያሳየ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት።
መርሃ ግብሩ ተፈጥሮን ከመጠበቅ ባሻገር በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም መፍጠሩንም ተናግረዋል።
ይህም አፍሪካ ራሷን በምግብ ከመቻል ባለፈ ለሌሎች መትረፍ እንደምትችል ጭምር ትምህርት የሚወሰድበት ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻልና በአካባቢ ጥበቃ እያከናወነች ያለው ስራም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተቸረው ስለመሆኑንም ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያና የመንግስታቱ ድርጅት በመተባበር በቅርቡ በአዲስ አበባ የሚያካሂዱት የምግብ ጉባኤ እንዲሁም በተመሳሳይ በቅርቡ በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለኢትዮጵያ ስራዎች እውቅና የሰጠ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
የአሁኑ ትውልድ የኢትዮጵያን የልመና ታሪክ በመቀየር ለመጪው ትውልድ የተሻለ ሀገር የመገንባት ሃላፊነት እንዳለበት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህ ደግሞ ዝቅ ብሎ መስራት ይገባል ብለዋል።
ከዚህ አኳያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያለ ልዩነት ለተሻለ ነገ ዜጎች በጋራ የሚያከናውኑት የሀገር ግንባታ አካል መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያዊያን ከነገ ጀምሮ በየአካባቢያቸው ችግኝ በመትከል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቅርበዋል።