ውል የተገባለት የመድኃኒት ፍላጎት እና አቅርቦት ሥርዓት አተገባበር ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።
የመድኃኒት እና የሕክምና ግብዓት አቅርቦት እንዳይስተጓጎል መንግስት ጠንካራ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ እና አሁንም የሕብረተሰቡን ፍላጎት የሚያሟላ ስራ ለማከናወን በጋራ መስራት እንደሚጠይቅ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ ተናግረዋል።
የመድኃኒትና የግብዓት አቅርቦት መቆራረጥ ፣ የበጀት እጥረት እና ሌሎች በጤናው ዘርፋ ያሉትን ችግሮች መቅረፍ የሚያስችል መድረክ መሆኑ ተገልጿል።
ውል የተገባለት የግዥ ስርዓት ስኬታማ እንዲሆን በጤናው ዘርፍ ያሉ ባለድርሻ አካላት በጥምረት መስራት ይጠይቃል ብለዋል የጤና ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ። የውይይት መድረኩ የሀገር ውስጥ የመድሃኒት ምርት አቅርቦት ውስንነት ለመቅረፍ አጋዥ መሆኑም ተነግሯል።
በጤናው ዘርፍ ያለውን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ እና ማህበረሰብ ተኮር አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስራዎችን ለማሻሻል የመድሃኒት አቅርቦት ስርዓት ቀልጣፋ ለማድረግ እና ጊዜውን የዋጀ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገልፅዋል።
በመድሃኒት አቅርቦት በኩል ያለውን ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሀገር ውስጥ አምራች ፣ አመራሮች እና ባለሙያዎች በልዩ ሁኔታ መስራት እንደሚጠይቅ ሚኒስትር ድኤታዋ ገልጸዋል።
በዳንኤል መላኩ