ተለዋዋጭ ከሆነው የአለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተመራቂዎች ራሳቸውን ተወዳዳሪ አድርገው ሃገራቸውንና ህዝባቸውን በሁሉም ዘርፎች እንዲያገለግሉ ፕሬዚዳንቱ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በ2017 ዓ.ም የተማሪዎች ምረቃ መርሃ ግብሩ 6849 ተማሪዎችን እያስመረቀ ነው።
በምረቃ መርሃግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታየ አጽቀ ሥላሴ ፣ የትምህርት ሚንስቴር ሚንስትርና የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ቻንስለር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፣ የኢፌድሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ቴዎድሮስ ምህረት ፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ፣ የአ/አ ዩንቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ፣ የተመራቂ ወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በ 1943 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ በሚል መጠሪያው በ33 ተማሪዎች ማስተማር የጀመረው የአሁኑ አንጋፋው አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በ75ኛ ዙር የምረቃ ዝግጅቱ 3334 በመጀመሪያ ዲግሪ ፣
2859 ፣ 352 በስፔሻሊቲና ሰብ ስፔሻሊቲ ፣ 304 በሶስተኛ ዲግሪ በአጠቃላይ 6849 ተማሪዎችን አስመርቋል። ከነዚህ ውስጥ 2483 ያህሉ ደግሞ ሴቶች መሆናቸው ተገልፅዋል።
በምረቃ መርሃግብሩ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታየ አጽቀ ሥላሴ ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ከ50 አመታት በፊት ከዚሁ ዩንቨርሲቲ እርሳቸውም ተመራቂ እንደነበሩ ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ ተመራቂዎች ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ቀዳሚ ሀገር ለማድረግ በህይወት በጉዟቸው ሁሉ ኢትዮጵያን ማስቀደም እንዳለባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ተለዋዋጭ ከሆነው የአለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተመራቂዎች ራሳቸውን ተወዳዳሪ አድርገው ሃገራቸውንና ህዝባቸውን በሁሉም ዘርፎች እንዲያሳድጉም ፕሪዘዳንቱ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ይታያል አጥናፉ