በዛሬው እለት “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ የ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ ደረጃ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
መርሐ-ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ባለፉት 6 ዓመታት መላ ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት በተሳተፉበት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር 40 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን እና ታሪክ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የሀገራችን የደን ሽፋን ከነበረበት 17 እጅ ወደ 23 እጅ አድጓል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ አበባ በ6 ዓመታት ውስጥ 85 ሚሊየን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ የመዲናዋም የደን ሽፋን ከ2.8 እጅ ወደ 22 እጅ ማደግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
በስድስት ዓመታት በከተማዋ የተተከሉ ችግኞች የፅድቀት መጠን ከ85 በመቶ በላይ መድረሱንም አንስተዋል፡፡
ይህ በመትከል ብቻ ሳይሆን በመንከባከብ እና በብዙ የጋራ ጥረት የተገኘ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ከንቲባዋ አያይዘውም፣ በተሠራው ሥራ የተራቆቱ መሬቶች አረንጓዴ ሆነዋል፣ የደረቁ ወንዞች እና ምንጮችም ማንሰራራት ጀምረዋል ብለዋል፡፡
በአፈር እና ሥነ ምህዳር ጥበቃ ሥራም ታላላቅ ውጤቶች መመዝገባቸውን የገለፁ ሲሆን፣ የተተከሉ ችግኞች በአሁኑ ሰዓት ጥላ፣ ውበት፣ የቱሪስት መስህብ፣ ምግብ፣ ውሃ፣ የሥራ ዕድልና ገቢ ማስገኘት መጀመራቸውን አብራርተዋል፡፡
በዚሀ ታላቅ ክብር ባለው ተግባር ላይ ያለመታከት የተሳተፋችሁ፣ የተከላችሁና የተንከባከባችሁ መላ ኢትዮጵያዉያን እና የከተማችን ነዋሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ፣ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች፣ አዲስ አበባ ታመሰግናችኋለች፣ መጪው ትውልድም ያመሰግናችኋል ብለዋል፡፡
ታሪክ መሥራታችንን እንቀጥላለን ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአረንጓዴ ሽፋናችን 30 በመቶ እስኪደርስ ድረስም ሳንታክት እንተክላልን በማለት አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
በማሬ ቃጦ