“በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከናወነ ባለው የ2017 የአረንጓዴ አሻራ መርሐ- ግብር በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በይፋ ተጀምሯል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የከተማዋን ገፅታ ውብና ማራኪ ለኑሮ ምቹ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ለዓመታት ጥሩ ገፅታ ያልነበራቸው የአዲስ አበባ ወንዞች ዛሬ ላይ ከተማ አስተዳደሩ እያከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ስራዎች ማንሰራራታቸውን አንስተዋል፡፡
የዘንድሮ ችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር የሚከናወነው በሸገር ወንዝ ከእንጦጦ ተራራ ጫፍ በመነሳት እስከ ፒኮክ በሚደርስ 21 ኪሎ ሜትር በሚሸፍን 860 ሄክታር መሬት ላይ መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ፣ በዚህ መርሐ-ግብር የተሳፉ አሻራቸውን በእነዚህ አካባቢዎች ማስቀመጣቸው ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ዓመት በኋላ እነዚህ የወንዝ ዳርቻዎች ከውበት ባለፈ ምግብ የምናገኝባቸው፣ የእግር ጎዞ የምናደርግባቸው እና ለመዝናኛነት እንዲውሉ በማድረግ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያሳዩ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በእነዚህ ወንዞች ዳርቻ የምንተክለው ምግባችን የሚሆኑ ፍራፍሬዎች ስለሆኑ በጥንቃቄ ልንተክል እና በቀጣይም ልንከባከብ ይገባል ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይ ወንዞቻችን ከብክለት ወደ ውበት እየመጡ ነው ያሉት ከንቲባዋ፣ መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብን ባህል ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በያለው ጌታነህ