ባለፉ ስድስት ዓመታት ሁሉም ኢትዮጵያዊ 40 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል ታሪክ ማኖሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ እንኳን ለ2017 ዓ.ም የጋራ አሻራ ማኖር አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
በከተማችንም ባለፋት ስድስት ዓመታት 6 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ ሽፋናችንን ከ 2 .8 ወደ 22 በመቶ ማድረስ ችለናል ሲሉም ገልጸዋል።
የፅድቀት መጠኑም ከ85 በመቶ በላይ መድረሱ መረጋገጡንም በመጠቆም፣ ይህ ለሁላችንም ኩራት ነዉ ብለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መረሐ-ግብራችን የተራቆቱ አካባቢዎች አረንጓዴ ለብሰዋል፤ የነጠፉ ወንዞች እና አካባቢዎች ማንሰራራት ችለዋል ሲሉም አክለዋል።
አዲስ አበባችንም ንፁህ ውብ እና የቱሪስቶ ገቢ ማግኛ መሆን ችላለች ያሉት ከንቲባዋ፣ በከተማ ደረጃ ዛሬ ያስጀመርነው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መረሀ ግብር ከሸገር ወንዝ በእንጦጦ ፓርክ አስከ ፒኮክ ወንዝ ዳርቻ የሚደርስ 21 ኪሎ ሜትር ሲሆን፤ 860 ሄክታር መሬት ይሸፍናልብለዋል።
በአጠቃላይ ከተማችን ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር 916 ሄክታር ቦታ አዘጋጅታለች ሲሉም ጠቁመዋል።
ውድ የከተማችን ነዋሪዎች በወንዝ ዳርቻዎች፣ በጤና ተቋማት ፣ በሃይማኖት ተቋማት ፣ በግል ሴክተሮች እና በጎዳናዎች ለምግብነት የሚውሉ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን በመትከል ኢኮኖሚያችንን እንገንባ በማለትም ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ህፃን አዋቂ፣ የተማረ ያልተማረ ሳንል ሁሉም ዜጋ በጋራ በመሆን እንትከል ስል ጥሪዬን አስተላልፋለሁም ብለዋል።
አዲስ አበባን ለመኖር ምቹ ለማድረግ መስራታችንን እንቀጥላለን ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ለዚህ መርሐ-ግብር ያለመታከት የሰራችሁ፣ የደገፋችሁ እና ተንከባክባችሁ ያሳደጋችሁ ታሪክ ያመሰግናቹሃል፤ ኢትዮጵያም ታመሰግናችኋለች ብለዋል።