የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የማንሰራራት ጉዞ እንዲሳካ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ሚኒስትሮች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ፣ የፌደራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት የችግኝ የተከላ መርሃ ግብር መካሄዱ ይታወቃል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ ሚኒስትሮች እንደገለጹት፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለቀጣዩ ትውልድ የተበረከተ ስጦታ መሆኑን ጠቁመው መርሃ ግብሩ ተጨባጭ ውጤቶች እየተገኙበት መሆኑንም አንስተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ደ/ር) እንዳሉት፤ ባለፉት 6 ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለኢኮኖሚው ፈጣን ዕድገት መመዝገብ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በመርሃ ግብሩ በርካታ የቡና ችግኞች መተከላቸውን ገልጸው ይህም ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ከቡና የምታገኘው የወጪ ንግድ ገቢ እየጨመረ እንዲመጣ ማስቻሉን ተናግረዋል።
አቮካዶን ጨምሮ የተለያዩ የፍራፍሬ ምርቶች ወደ ውጭ በመላክ ገቢ እየተገኘ መሆኑን ጠቅሰው፥ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ግቡን እንዲመታ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ውስጥ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው አረንጓዴ አሻራ ለትውልድ የሚበረከት ስጦታ ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ትሩፋቱ እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢኮኖሚው እንዲሳለጥ ከማገዝ ባለፈ ለኑሮ ምቹ ከባቢን የእየፈጠረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ አረንጓዴ አሻራ የከርሰ ምድርና ገጸ-ምድር ውሃ እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
መርሃ ግብሩ ምንጮች እንዲጎለበቱ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ደርቆ የነበረው የሀረማያ ሀይቅ ማገገምና ማንሰራራት የአረንጓዴ አሻራ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።
አፈር እንዳይሸረሸርና ግድቦች በደለል እንዳይሞሉም መርሃ ግብሩ ትልቅ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉም ተገልጿል።