የታይላንዳዊቷን አንገት ወግቶ የወጣው የዓሳ አጥንት

You are currently viewing የታይላንዳዊቷን አንገት ወግቶ የወጣው የዓሳ አጥንት

AMN- ሰኔ 23/2017

ከሳምንት በፊት ታይላንዳዊው ሱሪያን ቡፓአርት የሚስቱ አንገት ነጭ መርፌ በሚመስል ነገር የአንገቷን ቆዳ ሲወጋ የሚያሳይ ፎቶዎችን በፌስቡክ ገፁ ላይ አጋርቶ ነበር፡፡

ዓሳ መብላት ለሚወዱ የሀገሩ ሰዎች ማስጠንቀቂያ ይሆን ዘንድ ነበር ሱሪያን አስደንጋጩን ፎቶ በፌስቡክ ያጋራው፡፡ ይህን ያደረኩት ዓሳ ወዳድ ታይላንዳዊያን ዓሳ ከአጥንት የፀዳ ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው ሲል ለጋዜጠኞች ተናግሯል፡፡

ሚስቱ ሳንግ ላን የዓሳ ሾርባ እየጠጣች ሳለ ነበር በአጋጣሚ የዓሳውን አጥንት የዋጠችው፡፡ ከዚህ በኋላ አንገቷ ላይ ከባድ ህመም ተሰማት፣ ህመሙን ለማስታገስ ሩዝ እና የዳቦ ቅርፊት ተጠቅማ ልሻላት አልቻለም፡፡

ወደ ሆስፒታል ሄዳ የኤክስሬይ ምርመራ ብትደርግም ምንም አይነት እንግዳ ነገር አላሳየም፡፡

የኤክስሬይ ምርመራውን ተከትሎ በጉሮሮዋ ላይ ህመም ቢሰማትም ባሏ ሱሪያን እና ሳንግ ላን የዓሳው አጥንት እንደተነቀለ ተሰምቷቸዋል።

ህይወት እንደተለመደው ቀጠለች፡፡ ሳንግ ላን በጉሮሮዋ ላይ ያለውን ምቾት ማጣት ተላምዳው፣ ቁስሉም እንደሚድን አስባ ነበር፡፡

ነገርግን ከሁለት ሳምንታት በኋላ አንገቷ እንዳበጠ አስተዋለች። በዚህን ጊዜ ከታይሮይድ ዕጢ ጋር የተገናኘ ሊሆን እንደሚችል በመጠርጠር ዳግም ወደ ሆስፒታል ሄደች፡፡

ሁለተኛው የኤክስሬይ ህክምናም ምንም ያልተለመደ ነገር ስላላስተዋለ አንዳንድ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች ብቻ ተሰጣት፡፡

የተሰጣትን የህመም ማስታገሻ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ሳለች ሳንግ ላን የሚያሰቃያትን የህመሙን ቦታ ማሻሸት ጀመረች፡፡ በአንገቷ የውስጥ ቆዳ ላይ አንድ ሹል መርፌ መሳይ ነገር ሲወጋትም አስተዋለች።

ቦታውን ትንሽ ስትጫነው የነጭ መርፌ ጭንቅላት የአንገቷን ቆዳ ከውስጥ ወደ ውጭ በስቶ ወጣ፡፡

በሁኔታው የተደናገጡት ጥንዶች ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ሆስፒታል ተቻኮሉ፡፡ በሶስተኛው ዙር ህክምናም በሳንግ ላን አንገት ውስጥ ተቀርቅሮ የነበረ 2 ሴንቲ ሜትር የሚያህል የዓሣ አጥንት ዶክተሮች ማውጣት ቻሉ፡፡

ከዚህ በፊት እንደዚህ አይነት ነገር አጋጥሞት እንደማያውቅ ቀዶ ህክምናውን ያደረገው የዶክተሮቹ ቡድን ገልጿል፡፡

የዓሳ አጥንት በሰው አንገት ላይ ተጣብቆ በዚህ መልኩ ከውስጥ ወደ ውጭ ወግቶ ሲወጣ እምብዘዛም ያልተለመደ ነገር ነው፡፡

ያልጠበቀችው አስደንጋጭ ነገር ያጋጠማት ሳንግ ላንም ከእንግዲህ ለተወሰነ ጊዜ ወይም በቀሪ ዘመኗ ሙሉ በሙሉ ዓሳ ከመመገብ ልትቆጠብ እንደምትችል ለጋዜጠኞች መናገሯን አዲቲ ሴንትራል አስነብቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review