የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትናንትናው ዕለት ‘’በመትከል ማንሰራራት’’ በሚል መሪ ሀሳብ 7ኛውን ከተማ አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር አከናውኗል፡፡
በመርሐ-ግብሩ ከተሳተፉት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች መካከል የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ በሀገራችን እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በርካታ የቡና ችግኝ በመተከሉ የዘንድሮ የቡና ኤክስፖርት 2.5 ቢሊየን ዶላር መድረሱን እና ይህም የማይታሰብ የነበረ በዚህ መርሐ-ግብር ማሳካት የተቻለ መሆኑን ገልፀዋል…
ከዚህ ቀደም በቡና ኤክስፖርት ከአንድ ቢሊየን መዝለል የማይታሰብ ነበር ያሉት ሚኒስትሯ፣ በተጨማሪም የፍራፍሬ ዛፎችን በመትከላችን ኢትዮጵያ አቮካዶ እና ሌሎችንም የፍራፍሬ ምርቶች ወደ ውጭ እየላከች መሆኗን ተናግረዋል..
በሌማት ትሩፋት የተጀመርውን ስራ ለማጠናከር በንብ ማነብ ለማር ምርት ስራም አረንጓዴ ስነ-ምህዳር እንደሚያስፈልግ በማንሳትም፣ በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ውስጥ የታሰበውን ለማሳካት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ውጤት አሁን ፍሬውን እያየን ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ “በመትከል ማንሰራራት” የሚለው መሪ ሀሳብም በሚገባ እንደሚገልጸው አንስተፀዋል፡፡
መርሐ-ግብሩን ያስጀመሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የተለያዩ ባለስልጣናት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ ዲፕሎማቶች፣ አርቲስቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የተለያዩ ባለሞያዎች እና የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ አሻራቸውን አኑረዋል።
በያለው ጌታነህ