የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን 4ኛውን አዋርድ አካሄደ

You are currently viewing የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን 4ኛውን አዋርድ አካሄደ

AMN- ሰኔ 23/2017 ዓ.ም

የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን የድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን 5ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ እና 4ኛውን በስሙ የተሰየመ አዋርድ አካሂዷል፡፡

በአፋን አሮሞ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ ካሳረፉ ወጣት ድምፃዊያን መካከል ከፊት የሚጠቀሰው ድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ፣ በህይወት በነበረበት ወቅት በስፋት ከሚታወቅበት የሙዚቃ ሥራዎቹ ባሻገር ሰብዓዊ ተግባራትንም ያከናውን ነበር፡፡

ድምፃዊው ህይወቱ ካለፈ በኋላ በስሙ የተመሰረተው የሀጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽንም፣ የድምፃዊውን ራዕይ እያስቀጠለ ይገኛል፡፡

የሀጫሉ ሁንዴሳ ባለቤት እና የፋውንዴሽኑ መሥራች ወ/ሮ ፋንቱ ደምሴ፣ ፋውንዴሽኑ ድምፃዊው በህይወት እያለ የጀመራቸውን ሥራዎች እያስቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖችን በመርዳት፣ ለ60 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ በየዓመቱ ማቅረብ እና ሌሎችም በርካታ ሰብዓዊ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ፋውንዴሽኑ ዘንድሮ በተካሄደው 4ኛው አዋርድ ላይም በአፋን ኦሮሞ የሙዚቃ ቅንብር፣ በኬሮግራፊ፣ በድምፃዊነት እና በሌሎችም ዘርፎች የላቀ አስተዋፅዖ ያበረከቱ አርቲስቶችን ሸልሟል፡፡

ድምፃዊው ሰው ወዳድነትን፣ ፍቅርን፣ መደጋገፍን ትቶልን ያለፈ በመሆኑ ሁሌም በልባችን ይታሰባል ያሉት ደግሞ የመድረኩ ተሸላሚዎች ናቸው፡፡

በኪነ ጥበቡ ዘርፍም የሱን ፈለግ በመከተል የተሻለ ነገር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review