ችግር ፈቺ ስልጡን እጆች- ፌስታልን ለማስቀረት

You are currently viewing ችግር ፈቺ ስልጡን እጆች- ፌስታልን ለማስቀረት

AMN ሰኔ 24/2017

የፕላስቲክ ምርቶች የሚያደርሱት ዘርፈ ብዙ የጤና፣ የአካባቢ ብክለት፣ የንጽሕናና መሠል ተያያዥ ችግሮች ለስነ ምህዳር መዛባት አበርክቶአቸው ከፍተኛ ነው።

የፕላስቲክ ምርቶች ከፍተኛ ጉዳት ቢኖራቸውም ብዙ እና የማይናቅ አገልግሎት የሚሰጡም ናቸው።

አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቀምባቸው እነዚህ ምርቶች በቀላሉ መገኘታቸው እና ከተጠቀምንባቸው በኋላም በአግባቡ ስለማይወገዱ ችግር ሲፈጥሩ ይስተዋላል፡፡

በአፈር ውስጥ ተቅበረው በመቶ ዓመታት የማይበሰብሱ ከመሆናቸው ባሻገር በአፈር ውስጥ በቂ አየር እንዳይዘዋወር እና ምርት እንዳይኖር የሚያድርጉ መሆናቸውን ጥናቶች ያመላክታሉ።

ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ሀገራትም የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።

በመሆኑም የፕላስቲክ ምርት የሆኑ ከረጢቶችን በተኪ ምርቶች መቀየር ዋነኛው የመፍትሔ እርምጃም እየሆነ ነው።

በኢትዮጵያም ለችግሩ እልባት ለመስጠት በዘርፉ ተኪ ምርቶችን በማምረት ወደ ገበያ እያቀረቡና ወጣቶችንም እያሰለጠኑ ከሚገኙ ወጣቶች ውስጥ ሀይሌ አንለይ ተጠቃሽ ነው።

የችግሩን አስከፊነት በመረዳት ወደ ገበያው የተቀላቀለው ወጣት ሀይሌ የወረቀት ቦርሳ አሰልጣኝና አምራች በመሆን ከራሱ አልፎ ለሌሎችም የስራ እድል መፍጠር ችሏል።

በተለያየ መጠንና ዲዛይን የሚመረቱ የከረጢት ዘንቢሎችን ከ20 እስከ 60 ብር ለገበያ የሚያቀርበው ወጣት ሀይሌ እስከ 6 ኪሎ ግራም የመያዝ አቅም እንዳላቸው ይናገራል።

የወረቀት ማጣበቂያ፣ ዲዛይን፣ ቆረጣ፣ ገመድና የህትመት ቁሳቁሶች ለስራው የሚያስፈልጉ ግብአቶች መሆናቸውን የሚናገረው ወጣቱ ከ20 ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 50 ሺህ ብር በሚፈጅ ካፒታል በቀላሉ ስራውን መጀመር እንደሚቻል ያብራራል።

አሁን ላይ ቡቲኮች፣ ሆቴሎች፣ ግሮሰሪዎች እና ኮስሞቲክስ ቤቶችን ጨምሮ በርካታ ተጠቃሚዎች ምርቱን እየለመዱትና እየተጠቀሙበት ይገኛል።

ከደንበኞች ትዕዛዝ በመቀበል በቤት ውስጥ በአነስተኛ ቦታ የሚሰራ መሆኑ፣ ወጣቶች ይህን የስራ አማራጭ አርገው ቢይዙት በአጭር ጊዜ ትርፋማ መሆን እንደሚችሉም ይናገራል።

ለስራ የተነሳሳና ብቁ ችሎታ ያለው አንድ ሠው በቀን የተለያየ መጠን ያላቸው 80 የወረቀት ዘንቢሎችን መስራትና ገቢ ማግኘት ብቻም ሳይሆን፣የፕላስቲክ ምርቶችን በማስቀረትም ጉልህ ድርሻ ማበርከት ይቻላል ይላል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review