የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ለስትራቴጂክና ለከፍተኛ አመራሮች ምደባ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በምደባ ስነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው በሰጡበት የሥራ መመሪያ ከሪፎርሙ በፊት ምደባ ግልፀኝነት ባለው መልኩ ሲሰጥ እንዳልነበረ አስታዉሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሪፎርሙ ወዲህ ምደባዎችን ግልጽነት ባለው መልኩ በማካሄድ የፖሊስ አመራርና አባላቱ በልፋታቸው ልክ እንዲታዩና በሥራ አፈፃፀማቸው ማደግ እንዲችሉ መነሳሰትን የፈጠረ የምደባ አሠራር ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል አያይዘውም በምደባው በብቃታቸው እና በሥራ አፈፃፀማቸው ኃላፊነት የተጨመረላቸው፣ በዝውውር የተሻለ ተልዕኮ እንዲወስዱ የተደረጉ፣ በግዳጅ አፈፃፀም በተለይ በኦፕሬሽን ላይ የሀገርን ሰላም ለማጽናት የአካል ጉዳት ያስተናገዱ ከፍተኛ መኮንኖች በዚህ ምደባ ውስጥ መካተታቸው በግዳጅ ላይ ለተሰማራው የፖሊስ ሠራዊት መነሳሳትን ይፈጥራል ብለዋል።
በኃላፊነት ቦታ ለተመደቡ ከፍተኛ አመራሮች ከዘር፣ ከሀይማኖት፣ ከፖለቲካና ከሌብነት በፀዳ መልኩ ለሥራቸውና ለህሊናቸው ታማኝ በመሆን ሠራዊቱን እንዲመሩ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስተዳደር ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ነብዩ ዳኘ በበኩላቸው አመራሮቹ ለዚህ ከፍተኛ ኃላፊነት ሲታጩም በመስፈርትነት የተቀመጡ የአገልግሎት ዘመን፣ የማዕረግ ደረጃ፣ የትምህርት ዝግጅት እና የሥራ አፈፃፀም የታየ ሲሆን የብሄርና የፆታ ተዋጽኦን ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ሃለፊዉ አቶ ጄይላን አብዲ የተሾሙት ከፍተኛ አመራሮች ከወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ፣ ከወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ፣ ከፖሊስ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ እና ለኮሚሽነር ጀነራል ተጠሪ የሥራ ክፍሎች መስፈርቱን አሟልተው የተገኙ 3 ዋና መምሪያዎች፣ 1 ምክትል ዋና መምሪያ፣ 24 መምሪያ፣ 20 ምክትል መምሪያ ኃላፊዎች በአጠቃላይ በዝውውር እና በዕድገት 48 አመራሮች መሆናቸዉን ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ ተናግረዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ