በድጋፍ ሰልፉ ሕዝቡ ያስተላለፈው መልዕክት አመራሩ ለዘላቂ ሰላም መፅናትና ልማት ቀጣይነት ከፊት ሆኖ በመምራት በቁርጠኝነት ይበልጥ እንዲተጋ መነሳሳትን መፍጠሩን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ተናገሩ፡፡
በቅርቡ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ሰላምን የሚደግፍና ፅንፈኝነትን የሚያወግዝ ሕዝባዊ ሰልፍ መካሄዱ ይታወሳል፡፡
ሕዝባዊ ሰልፉ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች መካከል ጎንደር ከተማ አንዱ ሲሆን፤ የሰልፉ ተሳታፊ ነዋሪዎች በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጎንደር በከፍተኛ የልማት ሥራ ላይ እንደምትገኝ በመግለጽ ሰላሙንና ልማቱን ለማስቀጠል ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ከተማዋ ያገኘችው ዘርፈ ብዙ የልማት እድሎች ለህዝቡ የዘመናት የልማት ጥያቄ መሰረታዊ ምላሽ የሚሰጡ በመሆናቸው ለሰላም ዘብ በመቆም ልማቱን ለማስቀጠል የድርሻቸውን ለማበርከት መዘጋጀታቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ እንደገለጹት፤ ሕዝቡ የሰላሙም የልማቱም ባለቤት በመሆን ያበረከተው አስተዋጽኦ ለከተማው ሰላም መረጋገጥና ለልማቱ ስኬት የጎላ ፋይዳ አለው፡፡
ጎንደር ታሪኳን ያደሰ ውበቷንም የገለጠ የልማት፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆኑ በድጋፍ ሰልፉ ሕዝቡ ለመንግስት እውቅና የሰጠበት ታሪካዊ ዕለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሕዝቡ ሰላምና ልማትን አጥብቆ እንደሚፈልግና ይህን ለማደናቀፍ የሚሹ የጥፋት ተላላኪዎችን እንደሚያወግዝ ጥብቅ መልዕከት አስተላልፏል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ አመራሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሕዝቡን ለማገልገል ዝግጁ እንዲሆን አድርጓል ብለዋል፡፡
የከተማው ነዋሪ ሕዝብ በራሱ ተነሳሽነት በመኖሪያ አካባቢው እራሱን በማደራጀት ሰላሙን ለማረጋገጥ የወሰዳቸው እርምጃዎች ሰላም ፈላጊነቱንና ቁርጠኝነቱን በድጋፍ ሰልፉ ማረጋገጡን ተናግረዋል፡፡
መንግስት ህግ የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሕዝቡ በድጋፍ ሰልፉ ያስተላለፈው መልዕክት ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቁመው፤ የፀጥታ መዋቅሩ ሕዝቡ የሰጠውን ተልዕኮና ሃላፊነት በብቃት እንዲወጣ ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በፌዴራልና በክልሉ መንግስት ድጋፍ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ለሕዝቡ ፍትሃዊ የመልማት ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ አመራሩ እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች ለፍጻሜ እንዲበቁ ሌት ተቀን ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢንሼቲቭና አመራር ሰጪነት በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራ፤ የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትና ጥገና እንዲሁም የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሕዝቡ አዎንታዊ ድጋፍ ከሰጣቸው የልማት ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
ሕዝቡ ልማቱን አጥብቆ ከመደገፍ አንጻር የኮሪደር ልማት ስራው ስኬታማ እንዲሆን በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በጉልበቱ ጭምር ላበረከተው አስተዋጽኦ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ እውቅና ይሰጠዋል ነው ያሉት፡፡
በውጭና በሀገር ውስጥ የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆችና ባለሀብቶች ጭምር ከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን በመሳተፍ ልማቱን በገንዘብ ለመደገፍ ያሳዩት ተሳትፎም ጎንደር ወደ ቀደመ ገናና ታሪኳና ስሟ እንድትመለስ በር የከፈተ ነው ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የድጋፍ ሰልፉ አመራሩ በጊዜ የለኝም መንፈስ የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ በላቀ ፍጥነትና ጥራት እንዲሁም ቁርጠኝነት በተግባር በማስመስከር ሀገርና ሕዝብን የማሻገር ታሪካዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ታላቅ የቤት ስራ የሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡