በሞባይል ባንኪንግ ማጭበርበር ወንጀል የተሳተፉ ከ80 በላይ ዋነኛ ወንጀለኞችን በሕግ ተጠያቂ ማድረጉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ዘርፍ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል።
የወንጀል ምርመራ የኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ተወካይ ሙሊሳ አብዲሳ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሙስና፣ በህገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ በኮንትሮባንድና በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር የተጠረጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል በህግ ተጠያቂ መደረጋቸውን አስታውቀዋል።
ኮሚሽኑ ሕግን ለማስከበር በወሰደው እርምጃ 1ሺህ ተጠርጣሪዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው የቅጣት ውሳኔ መተላለፉን አንስተዋል።
በሞባይል ባንኪንግ ማጭበርበር የተሳተፉ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ በማድረግና የምርመራ መዝገብ በማጠናቀቅ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቀርቦ ክስ እንዲመሰረትባቸው መደረጉን ተናግረዋል።
እነዚህ ተጠርጣሪዎች ሀሰተኛ መታወቂያና በርካታ ሲም ካርዶችን በመጠቀም፣ ሆቴሎችና ማረፊያ ቤቶችን በመከራየት ዜጎችን በማጭበርበር ላይ ተሰማርተው የነበሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም በድርጊቱ ላይ የተሳተፉ ከ80 በላይ ዋነኛ ወንጀለኞች ላይ ምርመራ አድርጎ ክስ በመመስረት ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ መደረጉንም አብራርተዋል።
ከሀገር ውስጥና ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር በሽብር ወንጀል የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት እንዲሁም ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ለሕግ የማቅረብ ሥራ መከናወኑንም አስረድተዋል።
በዚህም ከ450 በላይ ተጠርጣሪዎች በሰነድና በሰው ማስረጃ በማጣራት ክስ እንዲመሰረትባቸው የተደረገ ሲሆን በህግ ተጠያቂ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ የተሳተፉ 143 ተጠርጣሪዎች ለሕግ መቅረባቸውን ጠቁመው ካናቢስ፣ ኮኬይንን ጨምሮ የተለያየ መጠን ያላቸው አደገኛ ዕጾች ዝውውር ወንጀል የተሳተፉ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ተጠያቂ ተደርገዋል ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ በበጀት ዓመቱ ከ6ሺህ በላይ የምርመራ መዝገቦች ምርመራ ተጠናቆ ለፍትህ ሚኒስቴር የተላከ ሲሆን በዚህም በሀገርና በህዝብ ላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።
አቶ ሙሊሳ አክለውም በዘረ መል/DNA/ ምርመራ ዘርፍም ከ300 በላይ የምርመራ ጉዳዮች መቅረባቸውን አስታውሰው ወቅቱንና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ምርመራ ተከናውኖ የተገኘው ውጤት ለሚመከተው አካል ተደራሽ ተደርጓል ብለዋል።
አጭበርባሪዎች ከባንክ የተደወለ በማስመሰል እያጭበረበሩ መሆኑን የገለጹት ሃለፊው ከባንክ ተደውሎ የሚሰጥ ምንም ዓይነት የባንክ አገልግሎት እንደሌለ ዜጎች ሊገነዘቡ እንደሚገባም አጽንኦት መስጠታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
ዜጎች የሚስጥር ቁጥራቸውን ለሶስተኛ ወገን አሳልፈው መስጠት የለባቸውም ያሉት አቶ ሙሊሳ ህብረተሰቡ ያጭበርባሪዎች ሰለባ እንዳይሆን ሊጠነቀቅ እንደሚገባ አመልክተዋል።