የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖርቹጋል ፖርቶ አዲስ በረራ ጀመረ

You are currently viewing የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖርቹጋል ፖርቶ አዲስ በረራ ጀመረ

AMN ሰኔ 25/2017

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖርቹጋል ፖርቶ አዲስ በረራ ጀምሯል።

አየር መንገዱ ወደ ፖርቶ በሣምንት አራት ጊዜ በረራ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

አየር መንገዱ ወደ ፖርቹጋል ፖርቶ ከተማ የሚያደርገውን በረራ አስመልክቶ ዛሬ ማምሻውን የማስጀመሪያ መርኃ ግብር ተከናውኗል።

በመርኃ ግብሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ በኢትዮጵያ የፖርቹጋል አምባሳደር ልዊሳ ፍራጎሶ እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ፥ አየር መንገዱ ወደ ፖርቶ የሚያደርገው በረራ ፖርቹጋልን ከአፍሪካ ጋር ለማስተሳሰር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ወደ አውሮፓ ለሚጓዙ መንገደኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችለውም ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ የፖርቹጋል አምባሳደር ልዊሳ ፍራጎሶ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ እና ፖርቹጋል ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ወዳጅነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

አየር መንገዱ ወደ ፖርቶ የጀመረው በረራም የሀገራቱን ወዳጅነት በኢኮኖሚና ህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር እንደሚያግዝም አውስተዋል።

አየር መንገዱ ዛሬ ያስጀመረውን በረራ ጨምሮ ከ145 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊዬን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review