በአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ጥራት ቁጥጥርና አደጋ አስተዳደር የሰለጠኑ 40 ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ተሰጣቸው

You are currently viewing በአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ጥራት ቁጥጥርና አደጋ አስተዳደር የሰለጠኑ 40 ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ተሰጣቸው

AMN ሰኔ 25/2017

በአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ጥራት ቁጥጥር እና አደጋ አስተዳደር የሰለጠኑ 40 የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ተሰጣቸው።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ የላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ስራዎችን በበላይነት ለመምራት በአዋጅ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋሙ ከዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ጋር በመተባበር በአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ጥራት ቁጥጥርና በአቪዬሽን አደጋ አስተዳደር ዙሪያ ስልጠና የወሰዱ 40 ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ አድርጓል።

አገልግሎት መስሪያ ቤቱ እንዳመለከተው፤ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ከአስራ ሁለት ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ አሰራሮች ላይ ባደረገው ኦዲት ሀገራችን ምንም ዓይነት የሴኪዩሪቲ ስጋት እንደሌለባት ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎም ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ጋር በተፈጠረው መልካም ግንኙነትና ትብብር ስልጠናው ከዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት በመጡ ባለሙያዎች ከሰኔ 9 እስከ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊሰጥ መሰጠቱ ተገልጿል።

ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀቱ አየር መንገዱ ተደራሽ በሚሆንባቸው ሀገራት ሁሉ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ የጥራት ቁጥጥር ተግባራትን ለማካሄድ የሚያስችል መሆኑን የገለጹት ከዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የመጡት አሰልጣኞች፤ ባለሙያቹ ስልጠናውን በስኬት ማጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል፡፡

ስልጣኞች ያገኙት ዕውቀት ተቋሙ ሀገራዊ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት ለመፈፀም የሚያስችለው ከመሆኑም ባለፈ፤ ሀገራችን ለአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ዘርፍ እየሰጠች ያለችው ልዩ ትኩረት ጉልህ ማሳያ ተደርጎም ሊወሰድ እንደሚችል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጠቁሟል፡፡

የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ጠንካራ የጥራት ቁጥጥር ትግበራ እና የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ዝግጁነት የእያንዳንዱ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት አባል ሀገራት ኃላፊነት መሆኑን ያስታወቀው አገልግሎት መስሪያ ቤቱ፤ ይህም የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን ደኅንነት በአለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጿል፡፡

በስልጠናው የተገኘውን ዕውቀት፣ ክህሎት እና የአስተሳሰብ ለውጥ በቀጣይ በአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ለተያዘው ራዕይ እና አጠቃላይ ተቋማዊ ስትራቴጂ ግብዓት አድርጎ በማዋል የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተመራጭነት ይበልጥ በማሳደግ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ አመልክቷል፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review