ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጋዝ ምርት ለገበያ ታውላለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 42ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው በ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያን የጋዝ ምርት አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ከዚህ ቀደም ጋዝ ለማውጣት ውል የሚገቡ ኩባንያዎች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ፍቃድ ለማግኘት እና ገንዘብ ማፈላለግ እንደሚሰሩ ነው የገለጹት፡፡
በመሆኑም አዳዲስ ኩባንያዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን አንስተዋል፡፡
በዚህም በሱማሌ ክልል የመጀመሪያው ምዕራፍ የጋዝ ምርት እንዳለቀ በመጠቆምም፣ ሁለተኛው ምዕራፍ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ማዳበሪያን በተመለከተም ኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ ባለቤት ለመሆን ግንባታ መጀመሩን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከባለ ሃብቱ አሊኮ ዳንጎቴ ጋር በመተባበር የሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ ከ40 ወራት በኋላ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያት በአፍሪካ ውስጥ ትልቅ የማዕድን ሀብት አላቸው ከሚባሉ ሀገራት አንዷ ብትሆንም፣ ነገር ግን የትኩረት እና የአመራር ማነስ ሀብቷን በተገቢው አልተጠቀመችበትም ብለዋል፡፡
ወርቅ ባለፈው ዓመት 4 ቶን መመረቱን በማስታወስ፣ ዛንድሮ ግን 37 ቶን አምርተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እዚህ ሁሉ ሀብት ላይ ተኝተን ነበር ስንለምን የነበረው በማለት ገልጸዋል፡፡
በገቢ ደረጃ ከወርቅ ባለፈው ዓመት 300 ሚሊየን ዶላር እንደተገኘ እና ዘንድሮ ግን 3.5 ቢሊየን ዶላር መገኘቱንም ነው ያመላከቱት፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ