6ኛው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 42ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የምክር ቤቱ አባላትም የተለያዩ ሃሳብና ጥያቄዎችን በማንሳት ላይ ይገኛሉ፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል አጠቃላይ የሃገሪቱ የሰለም ሁኔታን የተመለከቱ ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡
ጦርነት ይብቃ እያሉ፤ ጦርነት የሚያውጁና ራሳቸዉን እንደ ሰላም ሰባኪ የሚቆጥሩ አካላት ተፈጥረዋል፡፡
እነዚህ አካላት የኢትዮጵያን ትልቅነት ከሚቃወሙ የውጪ አካላት ጭምር ጋር አብረዉ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
እነዚህን አካላት ለማጋለጥ በመንግስት በኩል ምን እየተሰራ ነዉ ሲሉ የምክር ቤቱ አባላት ጠይቀዋል፡፡
የትግራይ ክልልን አሁናዊና አጠቃላይ የፖለቲካና የሰላም ሁኔታን በተመለከተም የህወሃት የቆየ የጦርነት ናፍቆት፤ ጸብ አጫሪነት እና በግጭት ምክንያት ራሱን የማቆየት ፍላጎት ዛሬም አልቆመም ሲሉ አንስተዋል፡፡
በዚህ ምክንያት ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት በስፋት እየተነሳ ነው፡፡
በአጠቃላይ በአሁናዊ የትግራይ ክልል የፖለቲካና የጸጥታ ሁኔታ ዙሪያ ማብራሪያ ቢሰጥበት ሲሉ የምክር ቤቱ አባላት ጠይቀዋል፡፡
ሃገራዊ ለዉጡን በተመለከተም ለዉጡ በሁሉም ዘርፍ ተስፋ ሰጪ ዉጤቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆንና ወደ ታለመዉ ግብ እንድትደርስ የመሃል ዘመን ፈተናዎችን በድል መሻገር እንደሚገባ ይወሳል፡፡
የመሃል ዘመን ወጥመድ ሲባል ምን ማለት ነዉ? እንዴትስ መሻገር ይቻላል? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ