ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰላምና የጸጥታ ችግር ዋነኛው መንስኤ የተሳሳተ የፖለቲካ አመለካከት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ናቸው።
ሰላምና ጸጥታን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ አንደኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የስንፍና ፖለቲካ የወለደው ችግር ነው ያሉ ሲሆን የስንፍና ፖለቲካ በሀገራችን ተንሰራፍቷል ብለዋል።
በዚያ ምክንያት ግጭት ጠብ፣ተቃርኖን ይወልዳል።ስራ አያውቁም ስራ አይወዱም ስራ አይሰሩም።አንድ ሰው ስራ ካልሰራ ደግሞ አልተማረም ማለት ነው። በስራ ተመንዝሮ የሚገኝ እውቀትና ልምድ ነው ሰውን አዋቂ የሚያሰኘው።
በእኛ ሀገር አርሶ አደር፣አርብቶ አደር ላብ አደር አለ፤ አሁን ደግሞ አውርቶ አደር ተጨምሯል። አውርቶ አደር ካላጋጩ ገቢ አያገኙም። እነዚህ ሰነፍ ፖለቲከኞች ስራ ሳይሰሩ፣ አገልግሎት ሳይሰጡ መብላት የሚፈልጉ ናቸው።ሁለተኛው መንስኤ የኃይል ፖለቲካ ነው።
ክላሽ ካነገትኩ ፍላጎቴ ይሳካል ብለው የሚያምኑ በህዝብ የተመረጠን መንግስት በኃይልና በወሬ እናፈርሳለን ብለው የሚያምኑ፣ በመግደል መሸነፍ እንጂ ማሸነፍ እንደሌለ የማያምኑ ናቸው።
በአንዳንድ አካባቢዎች ትምህርት አትማሩ፣ ማዳበሪያ አትውሰዱ ብለው ሰዎችን የሚገድሉ ሰዎች ካሉ ይህ እኩይ አላማ ነው።
ግድያ ሽንፈት ብቻ ነው የሚያመጣው ብሎ ማመን ያስፈልጋል።መቆም አለበት። ሶስተኛው ገፊ ምክንያት ድህነት ነው፤ ድሀነትን ካልቀነስን ስራ ካልፈጠርን ችግሩን መቅረፍ ያስቸግራል።ኋላቀርነት እና ዘረኝነት አባባሽ ችግሮች ናቸው። ዘረኝነት ሌላው ስር የሰደደ ችግር ነው። ዘረኝነት ልኩን ሲስት ለሰው ልጅ ጠንቅ ይሆናል።
እነዚህ እሳቤዎች የውጭ ጣልቃ ገብነት ታክሎበት የባንዳነት ስሪት ደግሞ በመስፋቱ ችግሩን አባብሶታል ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ስትጋጭ ትርፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ እሳት ጫሪ ጭልፊቶች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያውያንም እሳት ጫሪዎችን ማወቅና ማረም ያስፈልገናል፤ያን ጊዜ ችግሩ ይፈታል ነው ያሉት።