በበጀት ዓመቱ 4.2 ሚሊየን ህፃናት የቅድመ መደበኛ የትምህርት እድል እንዳገኙ እና ከነዚህም ውስጥ 29 ሺህ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናት መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትምህርትና ጤናን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ትምህርትን በሚመለከት በዚህ ዓመት 4.2 ሚሊዮን ህጻናት የቅድመ መደበኛ የትምህርት እድል እንዳገኙ እና ከነዚህም ውስጥ 29 ሺህ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናት መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ልክ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታና መምህራንን ማፍራት ላይም ሰርተናል ብለዋል።
የመምህራን ልማትን በሚመለከት ወደ 68 ሺህ መምህራን ሰልጥነዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ክረምት 80 ሺህ መምህራን በትምህርትና መማር ማስተማር ስልት ይሰለጥናሉ ብለዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር በኩል 30 ገደማ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ማህብረሰቡ በትምህርት ለትውልድ ባዋጠው ገንዘብ ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውን በመጠቆም፣ 46 ሚሊየን መፅሐፍት ታትመው በሁሉም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለአንድ ተማሪ 1 ማዳረስ መቻሉን ተናግረዋል።
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እገዛ ለማድረግ ሙከራ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ከጤና አኳያም በዘርፉ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከ22 ሺህ ገደማ የጤና ተቋማት መካከል 6 ሺህ ያህሉ ከለውጡ ወዲህ የተገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ምንም እንኳን የግል ዘርፍ የህክምና ተቋማት እየተስፋፉ ቢሆንም ተስፋ ሰጪ ጉዳዮች የመኖራቸውን ያህል አሁንም ችግር አለ ብለዋል።
ከመሰረተ ልማትና ከጤና ባለሙያዎች ጥያቄ አንጻር ምላሽ እየሰጠን መጓዝ ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህንን በማስፋት የጤና ስርዓቱን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
በሊያት ካሳሁን