ቤተክርስቲያኗ ይህንን ያረጋገጠችው የምክክር አጀንዳዎቿን ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባስረከበችበት መርሃግብር ላይ ነው፡፡
በኮሚሽኑ ጽህፅፈት ቤት በተከናወነው የአጀንዳ ርክክብ ሥነሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አባቶችና ምዕመናን በምክክር ሂደቱ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አንስተው በኮሚሽኑ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የቤተክርስቲያኗን አጀንዳዎች የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ ከሌሎች አባቶች ጋር በመሆን በጋራ አስረክበዋል፡፡
የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ በዚህ ወቅት ቤተክርስቲያኗ በምክክሩ ሂደት ላይ የነበራትን ቅሬታ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ትኩረት ሰጥተው በመፍታታቸው ችግሩ ተቀርፎ በአግባቡ እየተሳተፍን ነው ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ በሁሉም የምክክከር ሂደት እርከኖች እንድንሳተፍ እንዲሁም አጀንዳዎቻችንን በዚህ መልኩ አደራጅተን እንድናቀርብ እድል ስለሰጠንም በቤተክርስቲያቱ ስም እናመሰግናለን ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በ18 ገፆች ተቀንብቦ በቀረበው ሰነድ የተደራጁት የቤተክርስቲያኗ አጀንዳዎች ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም መረጋገጥ ጉልህ ሚና ያላቸው መሆናቸውንም ብፁዕ አቡነ ፍሊፖስ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ሀገርን የሚያሻግር ሥራ እያከናወነ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው የተጀመረው ሰላምን የማረጋገጥ ጉዞ እንዲሳካ ቤተክርስቲያኗ ከኮሚሽኑ ጎን በመሆን ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በርክክብ ስነስርቱ ላይ በኮሚሽኑ በኩል ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም እና ኮሚሽነር አምባሳደር ሙሐሙድ ድሪርም ተገኝተው የምስጋናና የአብረን እንስራ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡