በንግዱ ማህበረሰብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing በንግዱ ማህበረሰብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

AMN ሰኔ 26/ 2017ዓ.ም.

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት በመዘርጋት በንግዱ ማህበረሰብ የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ከመጪው ሀምሌ ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር ለማሸጋገር ባቀዳቸው አዳዲስ አሰራሮች ዙሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድና ዘርፍ ም/ቤት አመራሮች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ ቢሮው ከመጪው የግብር ማሳወቂያ ጊዜ ጀምሮ ፍትሃዊ የግብር አሰባበሰብ ስርዓትን ለመዘርጋት፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራሮች ለመከላከልና ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ በመስጠት ከግብር ከፋዮች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተለዩ አዳዲስ አሰራሮችን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልፀዋል።

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማልማትና ወደ ተግባር በማሸጋገርም የንግዱ ማህበሰረብ ከባለሙያዎች ስነ ምግባር፣ ከሌብነትና ብልሹ አሰራር ፣ ከፍትሃዊ የግብር አሰባሰብ ስርዓት አኳያ ለሚነሱ ቅሬታዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድና ዘርፍ ም/ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሐመድ በበኩላቸው ቢሮው የንግዱ ማህበሰረብ ቅሬታዎችን በአሰራር፣ በአደረጃጀትና በቴክኖሎጂ ለመፍታት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል፡፡

የቢሮው አመራር ለዓመታት በንግዱ ማህበሰረብ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎች በአጭር ጊዜ ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ እንዲመጡ በማድረግ ረገድ በኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቢሮው ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል እያደረገ ያለው ጥረት ም/ቤቱ ተባብሮ በመስራት እንዲሳካ የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡

የቢሮው ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለኤኤምኤን ዲጂታል እንደተናገሩት በዕለቱ ከንግዱ ማህበረሰብ ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review