ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሪፎርም እና ሁሉን አቀፍ እድገት መደገፍ የሚያስችል የአንድ ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ማርያም ሳሊም ተፈራርመዋል።
የሁለተኛው ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ እድገት ልማት ፖሊሲ ፕሮግራም(DPO) አካል የሆነው የፋይናንስ ስምምነት በእርዳታ እና በአነስተኛ ወለድ በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር(Concessional Loan) መልክ የሚሰጥ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የሪፎርም አጀንዳ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት እንደሆነም ገልጿል።
ፕሮግራሙ መንግስት የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት፣ የንግድ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ የሀብት ማሰባሰብ አቅምን ለማጠናከር፣ ተጠያቂነት የሰፈነበት እና ውጤታማ የመንግስት አገልግሎትን ለመፍጠር እንዲሁም የማህበራዊ አገልግሎቶቹን ዘላቂነት ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለውን ስራ የሚደግፍ መሆኑ ተመላክቷል።
የተጠቀሱት ስራዎች የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ እና መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ምሰሶዎች መሆናቸው ነው በመግለጫው የተገለጸው።
የኢትዮጵያ መንግስት የዓለም ባንክ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ቁልፍ ትኩረት በተሰጣቸው የሪፎርም መስኮች እያሳየ ላለው ገንቢ አጋርነት እና ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ልማት እውን የማድረግ የጋራ ግባቸውን ለማሳካት ያላቸውን ጠንካራ እና የፀና ትብብር የሚያመላክት እንደሆነም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።