ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የተገኘውን ስኬት ለማስቀጠል ሁሉም ኢትዮጵያዊ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

You are currently viewing ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የተገኘውን ስኬት ለማስቀጠል ሁሉም ኢትዮጵያዊ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

AMN- ሰኔ 27/2017 ዓ.ም

‎ኢትዮጵያውያ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ያገኘችውን ስኬት ለማስቀጠል ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዘንድሮው መርሐ- ግብርም የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሀገር አቀፉ አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ሰብሳቢ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ጥሪ አቀርበዋል፡፡

የሀገር አቀፉ አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ሰብሳቢ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር)፣ ከ7ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ጋር በተያያዘ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ኤፍ ኤም 96.3 ራዲዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ያለፉት 6 የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሮች የተጎዳ መሬትን በህብረተሰብ ተሳትፎ ማዳን እንደሚቻል አሳይተዋል ብለዋል ፡፡

‎ቀደም ያሉትን ዓመታት መረጃ በዋቢነት ያነሱት ዶክተር አደፍርስ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ 92 ሺህ ሄክታር መሬት ደን በየዓመቱ ይጨፈጨፍ እንደነበረ በማንሳትም፣ በየጊዜው በተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ተግባራት ቁጥሩን ወደ 27 ሄክታር መቀነስ መቻሉን አብራርተዋል=

‎ደን እንዳይጨፈጨፍ በመከላከል እና የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ስራውን በማጠናከር ከኖርዌይ የተገኘ የሳተላይት ምስልና ሲፎርና ሲያት በተሰኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት በተደረገ ጥናት የሀገሪቱ የደን ሽፋን ከ23 በመቶ በላይ መድረሱንም አስረድተዋል፡፡

‎ከእርሻ መሬቶች ብቻ 130 ቶን አፈር ከአንድ ሄክታር ይታጠብ እንደነበረ ያብራሩት ዶክተር አደፍርስ፣ ይህ አሀዝ አሁን ላይ ወደ 54 ቶን በሄክታር መሻሻሉን ጠቁመዋል፡፡

‎በሌላ በኩልም ከሌሎች የመሬት ክፍሎች ደግሞ 1.9 ቢሊየን ቶን አፈር ወደ ውሀማ አካላት ይገባ እንደነበርና አሁን ላይ ወደ 208 ሚሊየን ቶን መሻሻል መቻሉን ገልጸዋል፡፡

‎በሀገር አቀፍ ደረጃ በተከናወነው የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ፣ የደን ልማት፣ የአፈር ጥበቃና መሰል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ተግባራትም የሀገሪቱ ስነ ምህዳር ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰፊ ለውጥ እየታየበት እንደሚገኝ ዶክተር አደፍርስ አስገንዝበዋል።

‎የተገኙ ውጤቶችን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም ዜጋ በያዝነው ዓመት በሚደረገው የ7ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የነቃ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባም ነው የመርሐ-ግብሩ ሰብሳቢ ያስታወቁት፡፡

‎በሽመልስ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review