በትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ለማከናወን እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

You are currently viewing በትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ለማከናወን እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

AMN ሰኔ 27/2017 ዓ.ም

ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊዎች ልየታ መጠናቀቁን የጠቀሰው ኮሚሽኑ በትግራይ ክልልም በቅርቡ ለማካሄድ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው ብሏል።

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ በሰጡት መግለጫ የአጀንዳ ቀረጻ ለማካሄድም የአሰራር ሥርዓት ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰው የተሰበሰቡ አጀንዳዎች በየፈርጁ እየተደራጁ ነው ብለዋል።

ለዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ጉባዔው የሚመራበት የአሰራር ሥርዓት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ለዚህም የኮሚሽኑን አማካሪ ኮሚቴ ጨምሮ በየደረጃው የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ግብዓት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ለምክክር ጉባኤው አመቻቾችና አወያዮችን ለመምረጥ መስፈርቶች ተዘጋጅተው የመለየት ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በትግራይ ክልልም የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክሩን ተሳታፊዎች ልየታ ለማከናወን ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ምሁራን እና በአዲስ አበባ ነዋሪ ከሆኑ የክልሉ ተወላጆች ጋር ውይይት ማድረጉን አክለዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትም ትጥቃቸውን አውርደው በሰላማዊ መንገድ እንዲሳተፉ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የዳያስፖራ ማህበረሰብም በምክክሩ እንዲሳተፍ ዝግጅቶች መጀመራቸውን አንስተዋል።

የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባራት አሁንም መቀጠላቸውን ገልጸው፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት በቅርቡ የምክክር አጀንዳዎቻቸውን ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ወሳኝ የሆነው ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ ትግራይ ክልልን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካል በሂደቱ በመሳተፍ በጎ ሚና እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወቅ ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review