የመንግስትን በጀት በአግባቡና ግልጽ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል የተቋማት የእቃ ፍላጎት፣ አቅርቦትና ግዢ በኤሌክትሮኒክስ ስርዓት እንዲሆን ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰራ ይገኛል።
በ9 ተቋማት የጀመረው የኤሌክትሮኒክስ ግዢ ስርዓት አሁን ላይ 169 የፌደራል ተቋማት እና ቅርንጫፎቻቸውን ማዳረስ አስችሏል።
የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ እንዳሉት፣ በ2017 ዓ.ም በጀት ለሚመደብላቸው የፌደራል መስሪያ ቤቶች 590 ቢሊየን ብር የሚገመት ከ47 ሺህ 8 መቶ በላይ ጨረታዎች በግዢ ሂደት ላይ ይገኛሉ።
ከዚህ ውስጥም 308 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ግዢዎች ውል ሲፈጸም፣ የ281 ቢሊየን ግዢ በሂደት ላይ ነው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሯ።
እቃ አቅራቢዎች እና ገዢዎችን በቀላሉ በአንድ ሲስተም ያገናኘው የኤሌክትሮኒክስ ስርዓቱ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው የግዢ ስርዓት እንዲኖር እያስቻለ መምጣቱ ተነግሯል፡፡
ባለስልጣኑ በቀጣይም በዚሁ ስርዓት የሚያልፉ ተቋማትን ቁጥር በመጨመር በከተማ አስተዳደሮችና በክልሎች እንደሚተገብር ገልጿል።
ከ2018 በጀት ዓመት ጀምሮም የንብረት ሽያጭ በኤሌክትሮኒክስ ሲስተም እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ መሰረት ገልጸዋል፡፡
ባለስልጣኑ በግዢና ንብረት የህግ ማዕቀፎች ይዘትና በመንግስት ኤሌክትሮኒክስ የግዢ ስርዓት የተደረጉ የማሻሻያ ስራዎች ላይም ለመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷል።
በፍቃዱ መለሰ