ሩሲያ በአፍጋኒስታን ላለው የታሊባን አመራር እውቅና የሰጠች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች።
የአፍጋኒስታኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ካን ሙታኪ፣ በአፍጋኒስታን የሩሲያ አምባሳደር የሆኑትን ድሚትሪ ዚርኖቭ በሀገሪቱ ዋና ከተማ ካቡል አጊኝተው አነጋግረዋቸዋል።
በውይይታቸውም ሩሲያ ለአፍጋኒስታኑ ኢስላማዊ ኢምሬት በይፋ እውቅና መስጠቷን አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ የሩሲያን ውሳኔ ጥንካሬ የተሞላበት በማለት አወድሰውታል።
ታሊባን በፈረንጆቹ 2021 ወደ ስልጣን ከተመለሰበት ጊዜ ጀምሮ ምንም እንኳን በሰብአዊ መብት ጥሰት ሰፊ ትችቶችን ሲያስተናግድ ቢቆይም፣ ዓለም አቀፍ ህጋዊነት እና ኢንቨስትመንትን ሲፈልግ እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል።
ሩሲያ በፈረንጆቹ 2022 ከአፍጋኒስታን ጋር የተፈራረመችውን ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ስምምነት በኃይል፣ በትራንስፖርት፣ በግብርና እና መሰረተልማት ትብብሮች አጠናክራለች።
ከካቡል ጋር የተሟላ አጋርነትን ለመፍጠርም ታሊባንን ከአሸባሪነት መዝገቧ መሰረዟንም አስታውቃለች።
ባሳለፍነው ዓመት ሐምሌ ወር የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ታሊባን አጋራችን ነው ማለታቸውን ዘገባው አስታውሷል።
በሊያት ካሳሁን