ፕሬዚዳንት ትራምፕ የግብር ቅነሳን እና ወጪን በተመለከተ ያቀረቡት ረቂቅ ዕቅድ ፀደቀ

You are currently viewing ፕሬዚዳንት ትራምፕ የግብር ቅነሳን እና ወጪን በተመለከተ ያቀረቡት ረቂቅ ዕቅድ ፀደቀ

AMN- ሰኔ 27/2017 ዓ.ም

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአሜሪካ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብር ቅነሳ እና የወጪ ማዕቀፍን በተመለከተ ያቀረቡት ባለ 900 ገፅ ዕቅድ መፅደቁን ተከትሎ ለደጋፊዎቻቸው ደስታቸውን እየገለጹ ነው።

ህጉ ወታደራዊ ወጪን ማሳደግ፣ ስደተኞችን የማስወጣት መርሐ-ግብርን በገንዘብ መደገፍ እና የግብር ቅነሳን ለመደገፍ 4.5 ትሪሊዮን ዶላር መመደብን ጨምሮ አብዛኞቹን ትራምፕ በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት የገቧቸውን ቃሎች ያስከብራል ተብሏል።

የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤትም ለ29 ሰዓታት ያህል ከተወያየ በኋላ፣ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን የግብር ቅነሳ እና የወጪ ማዕቀፍ ረቂቅ ዕቅድን አጽድቋል።

በትናንትናው ዕለት በአሜሪካ የታችኛው ምክር ቤት የጸደቀው ዕቅድ፣ 218 ለ214 በሆነ ጠባብ ድጋፍ ማለፉም ነው የተነገረው።

212ቱም የምክር ቤቱ ዴሞክራት አባላት አዋጁን የተቃወሙ ሲሆን፣ የኬንታኪው ቶማስ ማሲ እና የፔንስልቬኒያው ብራያን ፊትስፓትሪክ ከሪፑብሊካኑ በኩል መቃወማቸው ተነግሯል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ህጉ አሜሪካ 250ኛ ዓመት ልደቷን በምታከብርበት ዋዜማ በመፅደቁ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው መናገራቸው ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ የህጉ መፅደቅ የሀገሪቱን እዳ ከፍ ያደርጋል፣ የጤናና የደሕንነት እንዲሁም የንፁህ ኃይል ድጋፍን ያዳክማል፤ በስደተኞች ላይ የሚደረገውን ቅስቀሳም ያጠናክራል በሚል ብዙዎችን እንዳሳሰበም ተመላክቷል።

ይሁንና ፕሬዚዳንቱ፣ የህጉን መፅደቅ ተከትሎ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር፣ ከሰዓታት በፊት ካሳካነው ድል የበለጠ ለአሜሪካ የልደት ስጦታ ሊኖር አይችልም ብለዋል፡፡

አያይዘውም ህጉ ለአሜሪካ በምድር የጠንካራ ድንበር፣ የጠንካራ ኢኮኖሚ፣ የጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ባለቤት እና በፕላኔቷ የትኛውም ሥፍራ ላይ ጠንካራዋ ሀገር መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው ማለታቸውን የአር ቲ ኢ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review