ስንፍናን መጠየፍ፣ በትጋት መስራት፣ የሚሰሩ እጆችን መደገፍ እና ማክበር የሰለጠነ ማህበረሰብ መገለጫዎች ናቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በመሆን ለአንድ ዓመት የሚቆይ “የሚሰሩ እጆች ወግ” የሚል የስራ ባህልን ለማዳበር እና የስራ ክቡርነት ግንዛቤን ለማሳደግ የሚረዳ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ከስራና ክህሎት ሚንስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ጋር በመሆን ይፋ አድርጓል።
ይህንኑ አስመልክቶ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ የምትቀየረው በመስራት ነው ብለዋል።
የዜጎችን ህይወት መቀየር የሀገር ክብር ነው፤ ስንፍናን በመጠየፍ እና የሚሰሩ እጆችን በማክበር ረገድ ከንግግር ያለፈ ውጤታማ ተግባር ከሁላችንም ይጠበቃል ሲሉም ገልጸዋል።
ሀገራችን ስንፍናን እና ልመናን መፀየፍ ይገባታል፤ ከቤተሰብ ጀምሮ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እና ተጽእኖ ፈጣሪዎች በአስተምህሮታችሁ ህዝባችን ተግቶ እንዲሰራ፣ ስራ አጥ ስራን ማማረጥ እዲተዉ፣ ስንፍናን አብዝቶ እንዲፀየፍ በድፍረት “ያልሰራ አይብላ” በማለት ማስተማር ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።
ወጣቶች የጊዜን ውድነት ተረድተው ጊዜያችው በማይረባ ነገር እንዳይባክን ማገዝ፣ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና ተስፋ ሰንቀው እንዲሰሩ ማበረታት ከሁላችንም የሚጠበቅ ሀላፊነት ነዉ ሲሉም አስገንዝበዋል።
ይህንን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ስራ ፈጣሪዎች፣ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም መላው ማህበረሰብ ከልብ እንዲሳተፍበት እና እንዲጠቀምበት ሲሉም ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ እና አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ግንዛቤ የሚያሻሽል እና የሚያበረታታ የቴሌቭዥን ፕሮግራም በማዘጋጀታቸውም ምስጋና አቅርበዋል።