የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ 7ኛዉን ዙር ከተማ አቀፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል በይፋ ማስጀመራቸዉ ይታወቃል፡፡
ይህንኑ ከተማ አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተከትሎ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎች፤ የመንግስትና የግል ተቋማት ፤ሌሎች ባለድርሻ አካላት አሻራቸዉን በማኖር ላይ ይገኛሉ፡፡
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎችም የ7ኛዉ ዙር ከተማ አቀፍ የአረንጓዴ ዐሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተሳታፊ በመሆን የተለያዩ ችግኞችን በመትከል ላይ ይገኛሉ፡፡
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ደቻሳ ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ ችግኞች መተከላቸዉን ገልጸዋል፡፡
የተተከሉት ችግኞች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ መሆናቸዉን የተናገሩት ሃለፊዉ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በመንከባከብ ለትውልድ ማሻገር ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ የተሳተፉት የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች አሻራውን በማኖር መደሰታቸውን ገልፀው የተከልናቸውን ችግኞች በመጠበቅና በመንከባከብ ለትውልድ የተሻለች ሀገር ማስረከብ ይኖርብናል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ የሀይማኖት አባቶች እና የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በመሀመድኑር ዓሊ