የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) 2ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።
ለሁለት ቀናት በሚደረገው በዚሁ ጉባኤ “በሀሳብ እንፎካከራለን ስለ ሀገር እንተባበራለን” በሚል መሪ ሀሳብ የፓርቲ አመራሮች ምርጫን ጨምሮ ሌሎች ክንውኖችም እንደሚደረጉበት ተገልጿል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትርና የኢዜማ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ኢዜማ ጠንካራ አቋም ያለው ለሀገር ቅድሚያ የሚሰጥ ድርጅት ነው ብለዋል፡፡
ኢዜማ በመላው ሀገሪቱ ተወካይ ያለው እንደ ሀገር መደገፍ የሚችል ፓርቲው ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በመጪው የምርጫ ጊዜም በሀሳብ የሚፎካከር ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ይሳተፋል ሲሉም ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአንድ ሀገር መሰረት በመሆናቸው በቅንጅት መስራት ይኖርባቸዋል ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
አገራዊ ለውጡን ተከትሎም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር በቅርበት መነጋገር መቻላቸው የፖለቲካ ስነ-ምህዳሩን ቀይሮታል ያሉት ደግሞ የብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለስ አለሙ ናቸው።
አክለውም ብልፅግና ፓርቲ ከኢዜማ ጋር መርህ ላይ በተመሰረተ ግንኙነት ለሀገር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ነው ማለታዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡