አዲስ አበባ በሀገሪቱ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ከ50 በመቶ በላይ ድርሻ እንዳላት ተጠቆመ
በሀገራት ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የከተሞች ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በተለይም ከጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት አንፃር ሲታይ ከተሞች ያላቸው አበርክቶ ይጎላል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሀቢታት (ዩ.ኤን ሀቢታት) በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2023 The Economic Role of Cities (የከተሞች ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ) በሚል ርዕስ ይፋ ያደረገው መረጃም ይህንኑ ያመላክታል፡፡
በዚህ መረጃ መሠረት፣ ከተሞች የሀገራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሞተር ናቸው። ፈጠራን በማቀጣጠል፣ ከፍተኛ የስራ ዕድል በመፍጠር፣ የንግድ እንቅስቃሴን በማፋጠን፣ የሀሳብ ልውውጥን በማመቻቸት፣ ተሰጥኦን በማጉላት፣ መልካም የስራ ባህልን በማዳበር፣ ውድድርን በማቀጣጠል፣ ምርትና ምርታማነትን በማላቅ የኢኮኖሚውን ዕድገት ግስጋሴ ያጧጡፋሉ፡፡ ያለ ከተሞች ዕድገት አንድም ሀገራት ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማምጣት ይቸገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ከተሞች ከ80 በመቶ በላይ የዓለምን ጥቅል ምርት (Global GDP) ያመነጫሉ፡፡ ዋናዎቹ 2 ሺህ የዓለም ከተሞች ከ75 በመቶ በላይ ድርሻ እንዳላቸው በመረጃው ተመላክቷል። ይህ አይነቱ አዝማሚያ በኢትዮጵያም ይስተዋላል፡፡ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ከተሞች 60 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው አውስተው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ከ50 በመቶ በላይ ድርሻ እንዳላት ተናግረዋል፡፡ ለመሆኑ ይህን ያህል ኢኮኖሚያዊ ድርሻ ባለው ከተማ ውስጥ እየተናከወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ትርጉም ምንድን ነው?
የምጣኔያዊ ሀብት ተንታኝ የሆኑት አቶ ኪሩቤል ሰለሞን በሰጡን ማብራሪያ ከተሞች ከገጠራማ ክፍሎች በላይ በኢኮኖሚያዊ ዕደገት ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ጠቁመው፣ ይህም ከጥንት ዘመናት ጀምሮ የሚታመንበትና በብርቱም የሚሰራበት ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃም በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛውን ድርሻ ያበረክታል፤ ስለዚህ በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ ግዙፍ የልማት ስራዎች ይህን አቅም የበለጠ አሟጥጦ የመጠቀም ዕድል እንደሚፈጥሩ በማብራሪያቸው አንስተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍ ያለ ፋይዳ ያላቸው ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች በስፋት ተሰርተዋል። ለአብነት የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ አብርሆት ቤተ መጻሕፍት፣ ሳይንስ ሙዚየም፣ የመንገድ እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በተለያዩ የከተማዋ አካባቢ ተገንብተው ለነዋሪው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ እንደዚሁም በኮሪደር ልማት ስራ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ፕላን ባለሙያ መስፍን አለሙ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማት ስራው ለአዲስ አበባ ከተማ ብሎም ለሀገሪቷ በርካታ ጥቅሞች አሉት፡፡ ዋናው በየአካባቢው ያሉትን መሰረተ ልማቶችን ማሻሻል ነው። ይህም የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችና ሌሎችም ደረጃቸውን በጠበቀ ሁኔታ የማሻሻል ስራ ተከናውኖበታል። እንደ አዲስ አበባ ላሉ ከተሞች ደግሞ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ማለት ትርጉሙ ብዙ ነው ይላሉ፡፡
ከተሞች የመሰረተ ልማት ዝርጋታቸው ምቹ ሲሆን ሰላማዊ፣ ከቆሻሻ የፀዳ ጤናማ አካባቢ እንዲፈጠር፣ የሰዎች እንቅስቃሴን የማይገድብ፣ ሰዎች ንፁህና ግልፅ የሆነ ቦታ ላይ እንዲንቀሳቀሱ ያስችላል፡፡ የኮሪደር ልማት ስራው የትራንስፖርት አገልግሎቱንም ምቹና ቀላል ያደርገዋል። ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈስሱ ያበረታታል። ይህ ደግሞ ለአዲስ አበባ ከተማ ኢኮኖሚያዊ እድገት የራሱ አስተዋፅኦ አለው፡፡
ከዚህ ባለፈ የትራፊክ መጨናነቅን ያስቀራል፣ የብዙሃን ትራንስፖርት እንዲስፋፋ ያደርጋል፤ የሥራ እድል ይፈጠራል፤ የልጆች መጫወቻ፣ የህዝብ ማረፊያ፣ መዝናኛ ስፍራዎች፣ አረንጓዴ ቦታዎች ስለሚበዙ ለህዝቡ ኑሮ ምች የሆነ ከተማ አንዲፈጠር ያደርጋል። እነዚህ ሁሉ ስራዎች ታዲያ በጥቅል ለመዲናዋም ይሁን እንደ ሀገር የሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከአባላቱ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የኢትዮጵያ ከተሞች 60 በመቶ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) መያዛቸውን ጠቅሰው፣ ከተማ ከተዘነጋ ይህን ያህል ሀብት ጥቅም ላይ እንደማይውል ተናግረዋል።
ከ50 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለው በአዲስ አበባ ከተማ እንደሆነም አውስተው፣ አዲስ አበባ ላይ ካልተሠራ ይህን ኢኮኖሚ መጠቀም እንደማይቻል ገልጸዋል። “ከተማን ማነቃነቅ አጠቃላይ ሀብታችንን ማነቃነቅ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ እስከ አሁን አዲስ አበባ ላይ በተሠራው ሥራ ምንም ብድር እንዳልተወሰደም ጠቁመዋል።
አያይዘውም ከተማ በራሱ ገቢ ራሱን ሲቀይር እንደ ቀላል መታየት እንደሌለበት ጠቅሰው፣ “አሁን ላይ ያለውን ለውጥ ሳይ እንዴት እዚህ ቆሻሻ ውስጥ እንደኖርን ይገርመኛል” ብለዋል። ትችት ላይ ያተኮሩ ሰዎች ለራሳቸው ከቆሻሻ ርቀው፤ ሌላው ሕዝብ ቆሻሻ ውስጥ እንዲኖር የሚያስቡ ሰዎች እንደሆኑ ተናግረዋል። ይህን የአዲስ አበባ ለውጥ ሌሎችም ሊተገብሩት እንደሚገባ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለዚህም ጅማ፣ ጎንደር እና ባሕር ዳርን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት፣ የቱሪዝም፣ የመንገድና መሰል ጉዳዮችን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ “እንደዚህ መገንባት፣ ማሳመር እየተቻለ ከተማችን በጉስቁልና ላይ የቆየችበት ዘመን የሚያሳፍር ነው” ነበር ያሉት። ከአራት ኪሎ አንስቶ እስከ እንጦጦ ያለውን የኮሪደር ልማት ስራን በማሳያነት ጠቅሰው፣ የቀድሞው የአካባቢው ገፅታ በጣም እንደሚያሳፍራቸው ተናግረዋል፡፡ “ላለፉት 100 ዓመታት እዚህ ቆሻሻ ውስጥ መኖራችን ነው የሚያሳፍረው፡፡ መቆሸሽ አይገባንም፡፡ ልጆቻችንም እንደዚህ አይነት ነገር እንዲያዩና ትልልቅ ጉዳዮችን እንዲተልሙ ማድረግ ይኖርብናል” ሲሉ ቁጭታቸውን ገልፀዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ከተሞች ለረጅም ዓመታት የቆዩበትን ቆሻሻና አረንቋ በማስወገድና ደረጃውን የጠበቀ ጽዱ አካባቢን እየፈጠረ ነው። አዲስ አበባ ላይ የመጣው የኮሪደር ለውጥ በራስ የፋይናንስ አቅም፣ በራስ እውቀት እና በዚህ አስገራሚ ደረጃ መገንባቱ ብዙዎችን እያስደነቀ ነው። የነዋሪዎችን አኗኗር አሻሽሏል። የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አካበቢዎች እየቀጠለ ያለ ነው ሲሉም አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እየተሰራ ያለው የኮሪደር ስራ ብቻ ነው ለሚሉ ሰዎች በሰጡት ምላሽ፣ “እነዚህ ሰዎች አንደኛ ስራ አያውቁም፣ ሁለተኛ ከተማ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ አይገባቸውም፣ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ የሀብቱን ምንጭ ስለማያውቁ ነው” ብለዋል፡፡ አያይዘውም በሌላ በኩል ደግሞ “ስራውን የሚያውቁት በፎቶ ብቻ ስለሆነ ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
የቱሪዝም ሴክተሩን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያም፣ ዘርፉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የመሸከም አቅም አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ለማሳያ ያህል በአዲስ አበባ ብቻ በፍሬንድሽፕ ፓርክ፣ በዩኒቲ ፓርክ፣ በሳይንስ ሙዚየምና በብሔራዊ ሙዚየም በዚህ ዓመት ብቻ በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች ተጎብኝተዋል ብለዋል፡፡
በዚህም ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መግኘቱንና እነዚህ ቦታዎች ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ13 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ስለመጎብኘታቸው አስረድተዋል፡፡ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በተሰሩ ስራዎችም የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር መጨመሩን አንስተው ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በአንድ ዓመት ውስጥ ተስተናግደዋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የቤት አቅርቦትን አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሲሰጡ የቤት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት በመንግስት፣ በግል እንዲሁም በመንግስትና በግል አጋርነት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡ ይህን ተከትሎም ባለፉት ዓምስት ዓመታት 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ቤቶች መገንባታቸውን አስታውሰው አሁን ላይ ከ265 ሺህ በላይ ቤቶች እየተገነቡ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡ በሌላ በኩል በክረምት በጎ ፈቃድ ከ100 ሺህ ያላነሱ ቤቶችን መገንባት መቻሉን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፉ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
“የዘንድሮው ዓመት ለኢትዮጵያ የማንሰራራት ዓመት ሆኗል፣ ዘንድሮ ትልልቅ ውጤቶች የተመዘገቡበት፤ አመርቂ ውጤቶች የታዩበት እና በኢትዮጵያ ታሪክ ታይተው የማያውቁ ድሎች የተጎናጸፍንበት ዓመት ነው”ም ብለዋል።
በሳህሉ ብርሃኑ