ፍልሰት በአግባቡ ከተመራ የማደግና አካታች የልማት ዕድልን እንደሚፈጥር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል።
አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ባካሄድነው የብሔራዊ የፍልሰት ምክር ቤት ዓመታዊ የምክክር መድረክ በፍልሰት ጉዳዮች ያከናወንናቸውን ተግባራት ገምግመናል ብለዋል።
ሀገራችን የውጭ ዜጎችን ተቀብላ በማስተናገድና ከለላ በመስጠት ረገድ ለረጅም ዘመናት የቆየና የዳበረ እሴት ያላት ናት፡፡
በአሁንም ጊዜ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብላ ጥበቃና ከለላ እያደረገች ትገኛለች፡፡
የፍልሰት ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት፣ የሠላምና ደህንነት እንዲሁም የፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲና የልማት ፖሊሲዎችን ቅርጽና ሁኔታዎችን በመበየን ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ አኳያ የሀገራችንን ሉዓላዊነት፣ ደህንነትና የመልማት ፍላጎት ከፍልሰተኞች ሰብዓዊ መብትና ክብር ጋር አመዛዝኖ መምራትን ይጠይቃል፡፡
ለዚህም የፍልሰትን በጎ ጎኖችን በማጎልበት ከኢኮኖሚ ሪፎርሙ ጋር አሰናስሎ መተግበር ይጠበቃል፡፡
ሀገራችን የፍልሰትን ጉዳይ በአስር ዓመቱ የልማት እቅዷ አካትታ እየተገበረች ትገኛለች፡፡
መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በቅንጅት መከላከል፣ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ ማጠናከር፣ ሕጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን ምህዳር ማስፋት ይገባል፡፡
በተለይም በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎቻችንን ደህንነታቸውን እና ክብራቸውን በጠበቀ አኳኋን መመለስና በዘላቂነት ማቋቋም እንደሚገባም በዛሬው ስብሰባችን አቅጣጫ አስቀምጠናል ሲሉ ገልጸዋል።