ካለፉት ምርጫ ሂደቶች የተሻሉ ተሞክሮዎችን በመውሰድ እና ችግሮችን በመለየት ለቀጣዩ ምርጫ የበለጠ ዝግጅት እየተደረገ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ገለጹ።
ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት የሪፎርም ስራቸውን አስመልክቶ የጋራ የውይይት መድረክ እያካሄዱ ነው።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ፣ የተቋማቸውን የሪፎርም ስራዎች አስመልክቶ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፣ ቦርዱ በህዝብና በመንግስት የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የነበሩበትን የአሰራር ክፍተቶች ለይቶ ለመፍትሄው ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በዚህም በህግና በአሰራር፣ በሰው ኃይልና አደረጃጀት ያሉ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ ሪፎርም ማድረጉንም አመልክተዋል።
ካለፉት ምርጫ ሂደቶች የተሻሉ ተሞክሮዎችን በመውሰድና ችግሮችን በመለየት ለቀጣዩ ምርጫ የበለጠ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
የሰባተኛውን ዙር ምርጫ ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም የምርጫ ሂደቱን ፈጣንና ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ የሞባይል መተግበሪያ በማበልፀግ የዕጩዎችንና የመራጮችን ምዝገባ በቴክኖሎጂ ለማከናወን ስራዎች ተጀምረዋል ነው ያሉት።
ተቋሙ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት በሰው ኃይልና በአደረጃጀት ራሱን ማብቃት የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የዕጩዎችና የመራጮችን ምዝገባ ለማካሄድ የሚያግዘው ቴክኖሎጂ አስተማማኝና በቦርዱ ባለሙያዎች የበለፀገ ሲስተም መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ምዝገባው በሞባይል መተግበሪያ፣ በቦርዱ ባለሙያዎች እገዛ እንዲሁም በማኑዋል መንገድ እንደሚከናወንም አመልክተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችና መራጮች ስለ ቴክኖሎጂው አጠቃቀም በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እገዛ ይደረግላቸዋል ብለዋል።
ለዚህ አሰራር የሚሆን አዋጅ ለምክር ቤቱ መቅረቡንም ነው ያመለከቱት።