ለአቅመ ደካሞች ቤት የመስራት፣ የማደስና የተቸገሩትን የመደገፍ ተግባር በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ቀነአ ያደታ (ዶ/ር) ገለጹ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማቱ በትግራይ ክልል ውቅሮ እና መቀሌ ከተሞች ያስገነቧቸውን 20 የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤቶች አስረክበዋል።
የቤቶቹን ግንባታ መጠናቀቅ ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ቀነአ ያደታ (ዶ/ር) በስፍራው በመገኘት ለነዋሪዎቹ አስረክበዋል።
ከዚሁ መርሃ-ግብር በኋላ ባደረጉት ንግግርም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር ) ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረው አቅመ ደካሞችንና የተቸገሩ ወገኖችን የማገዝ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማቱ በትብብር በውቅሮ 5 እንዲሁም በመቀሌ 15 በድምሩ 20 ቤቶችን በጥራትና በፍጥነት ገንብተው እና የቤት ውስጥ እቃዎችን አሟልተው ነዋሪዎች እንዲረከቡ መደረጉን አረጋግጠዋል።
በሁሉም መልኩ የመተጋገዝ፣ የመረዳዳትና አቅመ ደካሞችን የማገዝ ባህል እየዳበረ እና እየተጠናከረ ሊሆድ እንደሚገባም ማንሳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የትግራይ ክልል ሕዝብ የሰላምና የልማት አርበኛ መሆኑን አንስተው ፤ ልማትን በማጠናከርና ምርታማነትን በማሳደግ ትጋቱን አጠናክሮ በመቀጠል እንደ ሀገር ከድህነትና ተረጂነት ለመውጣት በሚደረገው ትግል ብርቱ ጥረት ማድረግ እንዳለበትም ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማቱ ትብብር ቤቶቹ በጥራትና በፍጥነት ተገንብተው የተበረከተላቸው ወገኖች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ይህንን ላስተባበሩ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።