በመዲናዋ ለ2018 በጀት ዓመት የተያዘው ረቂቅ በጀት ዘርፈ ብዙ ልማት ከማስቀጠል አኳያ ያለው ድርሻ የጎላ መሆኑን ምክር ቤቱ ያወያያቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ

You are currently viewing በመዲናዋ ለ2018 በጀት ዓመት የተያዘው ረቂቅ በጀት ዘርፈ ብዙ ልማት ከማስቀጠል አኳያ ያለው ድርሻ የጎላ መሆኑን ምክር ቤቱ ያወያያቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ

AMN- ሰኔ 28/2017 ዓ.ም

በመዲናዋ ለ2018 በጀት ዓመት የተያዘው ረቂቅ በጀት የከተማውን ነዋሪ በየደረጃው ተሳታፊና ተጠቃሚ በማድረግ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የሚያስከትሉት የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ችግሮች መግታት የሚያስችል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ያወያያቸው የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ የሕዝብ አስተያየት ሰብስቧል፡፡

በውይይቱም በምክር ቤቱ የመንግስት በጀት፣ ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ስንታየሁ ደስታ፣ ምክር ቤቱ የ2017 በጀት ዓመትን የአስፈጻሚ አካላት የዓመታዊ ዕቅድ ክንውን ሰሞኑን መገመገሙን ጠቁመዋል፡፡

የበጀት ግልጽነት ለመፍጠር፣ የሕዝብ ተሣትፎ ለማሳደግ እና ውጤታማነትን ለማረጋገጥ ይህን የሕዝብ አስተያየት ማሰባሰቢያ መድረክ ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

ለቀጣይ 2018 በጀት ዓመት ለመንግስት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ለመመደብ የታሰበው ረቂቅ በጀት፣ ከከተማዋ የልማት አቅጣጫ እና ዕቅድ ከማሳካት፤ የተጀመረውን ዘርፈ ብዙ ልማት ከማስቀጠል አኳያ ያለው ድርሻ የጎላ መሆኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በ4ኛ ዓመት 12ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ የከተማ አስተዳደሩ የ2018 ዓ.ም በጀት 350.12 ቢሊየን ብር ሆኖ ለምክር ቤት እንዲቀርብ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል፡፡

ረቂቅ በጀቱ በዋናነት ድህነት ቅነሳ ላይ በማተኮር ለዘላቂ ልማት፣ የስራ እድል ለሚፈጥሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች እና ከከተማው ነዋሪ በተለያየ መንገድ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለሚሰጡ አገልግሎትና አቅርቦት ድጎማዎችን ያከተተ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

ከአጠቃላይ በጀቱ ከ 70 በመቶ በላይ የሚሆነው ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የተመደበ ሲሆን፣ ቀሪው ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ቁጠባን መሰረት ላደረገ የመደበኛ የበጀት ጣሪያ እንዲሆን ካቢኔው መወሰኑም ይታወሳል።

ይህ ውሳኔ የከተማ አስተዳደሩ ሕግ አውጪ በሆነው ምክር ቤት ቀርቦ በጉባኤ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review