የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ልዩነት እንደማያግድ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ

You are currently viewing የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ልዩነት እንደማያግድ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ

AMN- ሰኔ 29/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ልዩነት እንደማያግድ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ፓርቲ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ፓርቲ “በሀሳብ እንፎካከራለን፤ ስለሀገር እንተባበራለን” በሚል መሪ ሃሳብ ከሰኔ 28/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ 2ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።

የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊ የስራ ኃላፊዎችና አባላትም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ሸገር ፓርክ ውስጥ ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ፓርቲ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የፖለቲካ ባህላችን በዜጎች ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር ይኖርበታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅም ከመወነጃጀል የጸዳ የፖለቲካ ባህልን በመገንባት በሀገር ጉዳይ ላይ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ርዕዮተ-ዓለማዊ የሃሳብ ልዩነት ተጠባቂና ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ ይህም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በትብብር ከመስራት እንደማያግድ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ፓርቲም የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለማዊ የሃሳብ ልዩነት ሳይገድበው ከገዥው ፓርቲ ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያውያንም በሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅምና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር እንዲኖረው በትብብር መስራት እንደሚኖርባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባል ግርማ ሰይፉ ፓርቲው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ወደ ሰለጠነ ምዕራፍ ለማሸጋገር ገንቢ ሚናውን እየተወጣ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያንም በሀገራቸው ጉዳይ ከሚፎካከሩባቸው ይልቅ የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ የሚተባበሩባቸው በርካታ አጀንዳዎች ያሏቸው ህዝቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የሚያጋጥማትን ጫና ለመቀነስ ኢትዮጵያ እየሰራችበት የሚገኝ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ የልማት አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።

የጅማ ዞን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ፓርቲ አባል ታደሰ ተፈራ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የጋራ የልማት አጀንዳችን ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ከሚገኘው የፓርቲው 2ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በጉለሌ ክፍለ ከተማ ሸገር ፓርክ አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖራቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሰኔ 20/2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review