የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም 2017 በነገው ዕለት በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል

You are currently viewing የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም 2017 በነገው ዕለት በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል

AMN- ሰኔ 29/2017 ዓ.ም

ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በስኬት በማስተናገድ ውጤታማ እየሆነች የመጣቸው አዲስ አበባ፣ በነገው ዕለት የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም 2017ን ማስተናገድ ትጀምራለች፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ በርካታ መሰረተ ልማቶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመዲናዋን ገፅታ በእጅጉ እየቀየሩና ማራኪ እያደረጓት መምጣታቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡

የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እና አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ከተገነቡ በርካታ መሠረተ ልማቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

መዲናዋ እነዚህን እና ሌሎች በኮሪደር ልማት ሥራዎች ያስመዘገበቻቸው ለውጦች፣ ለኮንፍራንስ ቱሪዝም ተመራጭ ከተማ እንድትሆን እያስቻላት መሆኑን ብዙዎች እየመሰከሩ ይገኛል፡፡

በነገው ዕለትም የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም 2017ን ማስተናገድ የምትጀምር ይሆናል፡፡

ፎረሙ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሴክሬታሪያት እና ከኤ ኢ ትሬድ ግሩፕ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው፡፡

ላለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም፣ አፍሪካ ያላትን እምቅ ሀብት ወደ ተጨባጭ አቅም ለመቀየር፣ የሥራ አጥነት ለመቀነስ፣ ፍትሃዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትንና አህጉራዊ ትስስርን ለማላቅ ያለመ ጉባኤ መሆኑን ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ጉባኤው ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ አድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የሚካሄድ ይሆናል፡፡

በጉባኤው የፌደራል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች የሚታደሙ ሲሆን፣ ከአፍሪካ እና ከመላው ዓለም የተውጣጡ ከ2 ሺህ በላይ የዘርፉ ተዋንያን ይታደማሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review