በበጀት ዓመቱ ከ151 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘት መቻሉን የአድዋ ድል መታሰቢያ አስታወቀ

You are currently viewing በበጀት ዓመቱ ከ151 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘት መቻሉን የአድዋ ድል መታሰቢያ አስታወቀ

AMN – ሰኔ 29/2017 ዓ.ም

የአድዋ ድል መታሰቢያ በበጀት ዓመቱ ከ151 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘት መቻሉን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግሩም ግርማ አስታውቀዋል፡፡

የአድዋ ድል መታሰቢያ በዋናነት የአድዋ ድልን ለማስተዋወቅ፤ ታሪክ ተሻጋሪ እንዲሆን እና በቀጣይነትም ሃገራዊ ገዢ ትርክትን ለመገንባት አላማን አድርጎ የተቋቋመ ቢሆንም፤ ከመታሰቢያ ጉብኝቱ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ እየተስፋፋ የመጣውን የኮንፈረንስ ቱሪዝም በማገዝ ረገድ ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ አቶ ግሩም ተናግረዋል፡፡

የአድዋ ድል መታሰቢያ በ2017 በጀት ዓመት ወደ 192 ሺህ 953 የሚጠጉ ጎብኚዎችን ማስተናገዱን ዋና ዳይሬክተሩ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ከነዚህም ጠቅላላ ጎብኚዎች መካከል ወደ 91 ሺህ 924 ወይም 47.8 በመቶ የሚሆኑት አዋቂ የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች፣ 64 ሺህ 223 ወይም 37.9 በመቶ የሚሆኑት ተማሪ ጎብኚዎች እንዲሁም ወደ 3 ሺ 115 ወይም 1.6 በመቶ የሚሆኑት የውጭ ሃገር ጎብኚዎች እንደሆኑ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በጎብኚዎች ረገድ የታቀደውን 92 በመቶ አሳክተናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በበጀት ዓመቱ 64 የሃገር ውስጥ እና 8 አለም አቀፍ መድረኮችን ለማስተናገድ ታቅዶ፤ ከታቀደው በላይ አፈፃፀም በማስመዝገብ 77 የሃገር ውስጥ እንዲሁም 14 አለም አቀፍ መድረኮችን ማስተናገድ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

በእነዚህ አጠቃላይ 91 መድረኮች፤ 94 ሺህ 228 ተሳታፊዎች መሳተፍ መቻላቸውም ተገልጧል፡፡

ተቋሙ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች አጠቃላይ 112 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማስገባት ታቅዶ ወደ 151 ሚሊዮን ብር ገቢ ማስገኘት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

40 ለሚጠጉ ቋሚ ሰራተኞች እንዲሁም በጊዜያዊነት በሚሰሩ ድርጅቶች ወደ 500 ለሚጠጉ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠር መቻሉንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review