የመሪዎቹ መገናኘት ከ21 የጦርነት ወራት በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ አዲስ ተስፋን አጭሯል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል ውይይት ከኔታንያሁ ጋር ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስቀድመው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ትራምፕ በጋዛ የተኩስ አቁም ጉዳይ ላይ ግፊት ማሳደራቸውን ተከትሎ ታዲያ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያምን ኔታንያሁ ዋሽንግተን ዲሲ ገብተዋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ከትራምፕ ጋር የማደርገው ውይይት ተስፋ ያደረግነውን ነገር ለማሳካት አስቻይ ይሆናል ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዳግም ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ኔታንያሁ ነጩን ቤተ መንግስት ሲጎበኙ ይህ 3ኛ ጊዜያቸው ነው፡፡
በእስራኤል እና ሀማስ መካከል የተጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነት በመሠረታዊ ልዩነቶች ምክንያት ለወራት ተቋርጦ ሰንብቷል፡፡
እስራኤል ታጋቾቿ እንዲለቀቁ እና ሀማሳም የጦር መሳሪያውን እንዲያስቀምጥ ትሻለች፡፡
ሀማስ በበኩሉ እስራኤል የጋዛን ምድር ሙሉ በሙሉ ለቃ ከወጣች እና ጦርነት ካቆመች በእጁ የሚገኙ ታጋቾችን ለመልቀቅ ዝግጁ ነኝ ሲል ከርሟል፡:
ሀማስ እስራኤል ዘላቂ ተኩስ አቁም እና ጦርነት እንደምታቆም በአሜሪካ በኩል ዋስትና እንደሚፈልግ ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡