በአራዳ ክፍለ ከተማ በሚኒልክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተገነባው የልጆች የእግርኳስ መጫወቻ ሜዳ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር እንዲሁም የከተማና የክፍለከተማ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል፡፡
ከ60 በመቶ በላይ ወጣቶች በሚኖሩባት አዲስ አበባ ይህን መሰረት ያደረጉ በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ያነሱት ዋና አፈ ጉባኤዋ፣ በዚህም የወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ግንባታዎች ግንባር ቀደም መሆናቸውን ገልፀዋል።
መዲናዋን በአፍሪካ ምቹና ተስማሚ የህፃናት ማሳደጊያ ለማድረግ በርካታ ስራዎች በተግባር እየታዩ ነው ያሉት ዋና አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ የተገነቡት የልጆች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለዚህ ማሳያ መሆናቸውንም አንስተዋል።
ልጆች በአዕምሮም በአካልም ብቁ ሆነው እንዲያድጉ ምቹ አካባቢን መፍጠር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም ዋና አፈ ጉባኤዋ በፕሮጀክቶቹ ምርቃ ላይ ተናግረዋል።
በራሄል አበበ