የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በራስ አቅም የተመሰረተ ሰብዓዊ አሻራን ለማኖር ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ አስገነዘቡ።
ማህበሩ ባለፉት 90 ዓመታት ኢትዮጵያ ችግር ላይ በነበረችበት ወቅት ሁሉ ላከናወናቸው ሰብዓዊና የጀግንነት ተግባራት በኢትዮጵያ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የማህበሩ 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል “90 ዓመታትን የተሻገረ የሰብዓዊ አገልግሎት አሻራ” በሚል መሪ ሀሳብ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የማህበሩ የበላይ ጠባቂ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ሳህለወርቅ ዘውዴና ሙላቱ ተሾመ(ዶ/ር)፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶን ጨምሮ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የማህበሩ የበላይ ጠባቂ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ማህበሩ በኢትዮጵያ ፈተናዎች የተወለደ የርህራሄና የበጎነት መገለጫ ነው ብለዋል።
የማህበሩ ተግባርም ከኢትዮጵያ የሉዓላዊነትና የሰብዓዊነት ተግባር ጋር የተቆራኘ መሆኑን አንስተዋል።
ማህበሩ በቀጣይ 100 ዓመቱን ሲያከብር፣ ህዝባዊ መሰረቱን አስፍቶ፣ በእሳቤ ጥራት፣ በገንዘብና በእውቀት ራሱን ችሎ፣ ዘመኑን የዋጀ ህጋዊ ማዕቀፍ አበጅቶ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጣናውና በአፍሪካ የሰብዓዊነት ተምሳሌት የሆነ ታላቅ ተቋም ሆኖ ሊገኝ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት አበራ ቶላ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በመላ ሀገሪቱ መዋቅሩን በማስፋት የሰብዓዊ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
ማህበሩ ዓላማውን ማሳካት የሚያስችለውን አቅም እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዚህ ደግሞ የመንግስት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ማህበሩ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የአባላቱን ቁጥር 20 ሚሊየን በማድረስ ወጪውን በራስ አቅም የመሸፈን እቅድ መያዙንም አመልክተዋል።