ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ለነሐሴ የተራዘመው ቀነ ገደብ ከማለቁ በፊት ከአሜሪካ ጋር መደራደር እንደሚፈልጉ አስታወቁ

You are currently viewing ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ለነሐሴ የተራዘመው ቀነ ገደብ ከማለቁ በፊት ከአሜሪካ ጋር መደራደር እንደሚፈልጉ አስታወቁ

AMN- ሐምሌ 1/2017 ዓ.ም

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለ90 ቀናት ቀነ ገደብ ያስቀመጡለት የውጭ ንግድ ታሪፍ፣ አስከ ነሐሴ መራዘሙን ተከትሎ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ አዲሱ ቀነ ገደብ ከመድረሱ በፊት መደራደር እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በ14 ሀገራት ላይ ከአስተዳደራቸው ጋር ስምምነት የማይገቡ ከሆነ፣ ከ25 እስከ 40 በመቶ የሚደርስ የውጭ ንግድ ታሪፍ ሊጣልባቸው እንደሚችል ለሀገራቱ ማስጠንቀቂያ ያዘለ ደብዳቤ ልከዋል።

ይህንንም ተከትሎ የእስያ የትላልቅ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑት ሀገራት ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ መደራደር እንደሚፈልጉ ማስታወቃቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።

ከሶስት ሳምንታት በኋላ ተፈፃሚ ይሆናል ተብሎ ቀነ ገደብ በተቀመጠለት አዲሱ ታሪፍ፣ ጃፓን ለተሽከርካሪ ኢንዱስትሪዋ የታሪፍ ቅናሽ የምትፈልግ ሲሆን፣ በግብርና ዘርፍ ላይ ግን እንደማትደራደር አስታውቃለች።

ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ድርድርን ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች።

አዲሱ ታሪፍ የአሜሪካ የንግድ አጋር የሆነው የአውሮፓ ህብረትንም የሚነካ ሲሆን፣ ህብረቱም ያለው አማራጭ ከቀነ ገደቡ በፊት መደራደር፣ አሊያም ለአፀፋዊ ምላሽ መዘጋጀት መሆኑን አስታውቋል።

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review