የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት የአውሮፕላን ማረፊያ መሠረተ ልማት መስፋፋት የሀገራዊ እድገትን የሚያሳልጥ ነው።
በተለይ ምርታማነትን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የዘመነ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት የማይተካ ድርሻ አለው ብለዋል።
ዛሬ አገልግሎት የጀመረው የቴፒ መለስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ የትራንስፖርት አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ለአካባቢው ሁለንተናዊ ዕድገት ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑን አመልክተዋል።
ይህም መንግስት ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የትራንስፖርት አማራጭ መሠረተ ልማቶችን ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የሚያረጋግጥ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የቴፒ መለስተኛ አየር ማረፊያ አገልግሎት መስጠት ካቆመ 30 ዓመታት ማስቆጠሩን ገልጸዋል።
አሁን ላይ መንግስት ይህን ዳግም ማስጀመሩ የልማት ፍትኃዊነትን በማረጋገጥ የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት ተጨማሪ አቅም እንዳለው ተናግረዋል።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ አየር ማረፊያው በ1950 ዓ.ም ተገንብቶ ከ1990 በኋላ አገልግሎት ሳይሰጥ እንደቆየ አብራርተዋል።
ዳግም አገልግሎት እንዲሰጥ ከኅብረተሰቡ በተሰበሰበ 6 ሚሊዮን ብር የጥገና እና የአጥር ሥራ መከናወኑንም መጠቆማቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተያያዘም በዛሬው ዕለት የቴፒ ቡና ቅምሻና ሰርቲፊኬሽን ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።